ኢራናውያን አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ድምጽ እየሰጡ ነው

የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ድምጽ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ድምጽ ሲሰጡ
ታትሟል

ሐሰን ሩሃኒን የሚተኩ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ኢራናውያን ዛሬ አርብ ድምጽ እሰጡ ነው።

ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት መሠረት የፍትህ ሥርዓቱን በበላይነት የሚመሩት ወግ አጥባቂ የሺአ መሪ ኢብራሂም ራይሲ ያሸንፋሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

የቀድሞው ማዕከላዊ ባንክ ገዥ አብዶልናስር ሄማቲ ተቀናቃኛቸው ናቸው።

በርካታ ተፎካካሪዎች እንዳይወዳደሩ መታገዳቸው ራይስን ያለ ከባድ ተፎካካሪ እንዳስቀራቸው በመጥቀስ ተቃዋሚዎች እና አንዳንድ የለውጥ አራማጆች ሕዝቡ እንዳእመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐይማኖታዊው መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ አርብ ማለዳ ዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ሰዎች እንዲመርጡ አበረታተዋል።

"እያንዳንዱ ድምጽ ዋጋ አለው። ይምጡና ፕሬዝዳንትዎን ይምረጡ። ይህ ለአገርዎ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ ከሦስት ዓመት በፊት ከኢራን ጋር የደረሰችውን የኒኩሌር ስምምነትን ወደ ጎን አድርጋ ማዕቀቦችን ወደነበሩበት ከመለሰችበት ጊዜ ጀምሮ በደረሰው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በኢራናውያን ዘንድ ሰፊ ቅሬታ አለ።

ከተፎካካሪዎቹ አንዱ ቢያሸንፉ በኢራን እና በዓለም ኃያላን መካከል ስምምነቱን እንደገና ለማደስ ዓላማ ያደረገው ድርድር ያደናቅፋል ተብሎ አይታሰብም።

ለዘብተኛው ሩሃኒ ከምዕራባውያን ጋር ለመግባባት ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም ለሁለት ተከታታይ አራት ዓመታት የሥልጣን ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸውን በድጋሚ መወዳደር አይችሉም።

ዕጩዎቹን ማን አፀደቀ?

40 የሚሆኑ ሴቶችን ጨምሮ ወደ 600 የሚጠጉ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው ተመዝግበዋል።

የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ብቃት በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ያለው ያልተመረጠ አካል ሲሆን 12 የሕግ ባለሙያዎች እና የሐይማኖት ምሁራንን የያዘ ነው። በዚህ አካል ሰባት ዕጩዎች ለፕሬዝዳንትነት እንዲወዳደሩ ፈቃድ ሰጠቷል።

እንዲወዳደሩ ካልተፈቀደላቸው ታዋቂ ዕጩዎች መካከል የሩሃኒ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዝዳንት ኢሻቅ ጃሃንጊሪ እና ወግ አጥባቂውና የፓርላማ አፈ ጉባኤ የነበሩት አሊ ላሪጃኒ ይገኙበታል።

ሐሙስ ድረስ እንዲወዳደሩ ከተፈቀደላቸው ዕጩዎች መካከል ሦስቱ (የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊው ሰዒድ ጃሊሊ፣ የፓርላማ አባሉ አሊሬዛ ዛካኒ እና የለውጥ አራማጁና የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞህሰን መህላራሊዛዴህ) ራሳቸውን አግልለዋል።

ጠንካራ አቋም ያላቸው ጃሊሊ እና ዛካኒ ሁለቱም ራይስን ደግፈው የቆሙ ሲሆን መህላራሊዛዴህ ደግሞ የውጥ ኃይሉን "አንድ ለማድረግ" እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ይህም ለሔማቲ ግልጽ ድጋፍ መስጠት ነው ተብሏል።

አንድ ተወዳዳሪ በአንደኛው ዙር ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ካላገኘ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ይካሄዳል።

በውድድሩ እነማን ይሳተፋሉ?

ኢብራሂም ራይሲ

የ60 ዓመቱ ሐይማኖታዊ መሪ አብዛኛውን የሥራ ዘመናቸውን በዐቃቤ ሕግነት አገልግለዋል። ባለፈው ምርጫ በሩሃኒ ከተሸነፉ ከሁለት ዓመታት በኋላ እአአ በ2019 የፍትህ ዋና ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

ራይስ ሙስናን ለመዋጋት እና የኢራንን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የተሻሉት ሰው እንደሆኑ እያስረዱ ነው።

ብዙ ኢራናውያን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በ1980 ዎቹ በፖለቲካ እስረኞች የጅምላ ግድያ ላይ ሚና አለቸው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አብዶልናሰር ሔማቲ

የ64 ዓመቱ ባለሙያ እአአ በ2018 የኢራን ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩ ሲሆን ዕጩ ከሆኑ በኋላ ግን ከኃላፊነት ተነስተዋል።

በሩሃኒ እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት መሐሙድ አህመዲነጃድ ስር መሾማቸው በኢራን ያሉትን ሁሉንም አንጃዎች በጋራ የማሠራት ብቃት እንዳለቸው ማስረጃ ተደርጎ ታይቷል።

የአሜሪካ ማዕቀብ የኢራን ገንዘብ ምንዛሬ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማቃለል ባለመቻላቸው ከሌሎቹ ዕጩዎች ትችት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል።

ሞህሲን ረዛይ

የ66 ዓመቱ ረዛይ መንፈሳዊውን መሪ በበላይነት የሚያማክሩና በሕግ ጉዳዮች ላይ በሚነሱ አለመግባባቶች የመጨረሻ የመዳኘት ስልጣን ያላቸው የምክር ቤት ጸሐፊ ናቸው።

እአአ ከ1988-88 በኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ወቅት የእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ቡድን አዛዥ ነበሩ። መከላከያ ኃይሉን ከለቀቁ በኋላ ለሦስት ጊዜያት ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ ሆነው ተወዳድረዋል።

አሚርሆሴን ቀዚዛዴህ ሃሸሚ

አሚርሆሴን ቃዚዛዴህ ሃሸሚ የአንገት በላይ የቀዶ ጥገና ሐኪም ናቸው። ከ2008 ጀምሮ የፓርላማ አባል የነበሩ ሲሆን ከግንቦት ወዲህ ደግሞ ተቀዳሚ አፈ-ጉባኤ ናቸው።

የ50 ዓመቱ ዕጩ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል በዕድሜ ትንሹ ናቸው።

የሕዝብ ተሳትፎ ለምን አስፈላጊ ሆነ?

80 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኢራን 59 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ብቁ ናቸው።

በ2017ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሳታፊዎች 73 በመቶ ቢሆንም በመንግሥት በሚደገፈው የኢራን ሰቱደንትስ ፖሊንግ ኤጀንሲ ባደረገው ጥናት ግን በአርቡ ምርጫ 42 በመቶዎቹ ብቻ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ጠቁሟል።

ይህ እአአ ከ1979ቱ እስላማዊ አብዮት በኋላ በኢራን ከተደረጉት ምርጫዎች ይህ ዝቅተኛ ተሳትፎ የሚኖረው ሲሆን ተመራጩም የመራጮች ቁጥርን እንደ ድጋፍ ስለሚያየው ችግር ሊደቅን ይችላል።

ሩሃኒ ሐሙስ ለኢራናውያንን "የተቋም ወይም የቡድን ጉድለቶች" ድምጽ ከመስጠት እንዳያስቆሟቸው ነግረዋቸዋል።

"ለጊዜው ስለነገ ለቅሬታዎች አናስብ" ብለዋል።