ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና በአዲሱ ጠፈር ጣቢያ የመጀመሪያ የባለሙያዎች ቡድን ላከች
ቻይና በገነባችው አዲሱ የጠፈር ጣቢያ ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ጠፈርተኞች ወደ ምህዋር ልካለች።
ወደ ጠፈር የተላኩት ሶስቱ ቻይናውያን በጠፈር ጣቢያው የሚኖራቸውን ተልዕኮ ለማከናወን 3 ወራትን ከመሬት በላይ 380 ኪሎ ሜትር ባለውና ቱናሄ ሞዱል በተሰኘው የቻይና አዲሱ የጠፈር ጣቢያ ላይ ይቆያሉ።
ይህ የጠፈር ጉዞ በቻይና ጠፈርተኞች ታሪክ ረጅሙ የሚሆን ሲሆን ከአምስት ዓመታት በኃላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
'ሹንዙ 12' የሚል ስያሜ የተሰጠው ተልዕኮ የሚፈጽሙት ጠፈርተኞችን የያዘውና 'ሎንግ ማርች' የተሰኘችው ሮኬት 'ጎቢ' ከተሰኘው የቻይና በርሀ ውስጥ ከሚገገኝ ማዕከል በተሳካ ሁኔታ ከምድር ተመንጥቋል።
ታዲያ ይህ የቻይና የጠፈር ተልዕኮ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላት አቅምና ብቃት እያደገ መምጣቱን ማረጋገጫ ነው ተብሏል።
ቻይና ባለ 6 እግር ሮቦት ወደ ጠረፍ በመላክ ባለፉት 6 ወራት ከጨረቃና ከማርስ የድንጋይና የአፈር ናሙናዎችን ወደ ምድር ይዛ መጥታለች።
ይህም እጅግ የተወሳሰበና ፈታኝ የጠፈር ላይ ክንውን መሆኑ ተሰምቷል።
የዚህ የጠፈር ተልዕኮ የመጀመሪያ ግብ በጠፈር ላይ የሚገነባ ጣቢያን ወደ ስራ ማስገባት ነው።
የተልዕኮው መሪ "አዲሱን ቤታችንን በጠፈር ላይ ማቋቋም እና በተከታታይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፈተሽ ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ተልዕኮው ከባድ እና ፈታኝ ነው ፡፡ በጋራ በመስራት ፈተናዎችን ማለፍ እንደምንችል አምናለሁ" ብለዋል።