ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም በጥልቀቱ ቀዳሚ የሆነ የውሃ ገንዳ በእንግሊዝ ሊገነባ ነው
ለባህር እና ለጠፈር ምርምር የሚያገለግል በዓለም በጥልቀቱ ቀዳሚ የሆነ የውሃ ገንዳ በእንግሊዝ፣ ኮርንዎል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በ 150 ሚሊዮን ዩሮ የሚገነባው ፕሮጀክት በኮርንዌል አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው ኤሮሃብ ኢንተርፕራይዝ ዞን የሚያርፍ ሲሆን 50 ሜትር ጥልቀት ያለው ገንዳ የሚይዝ የውሃ ማዕከል ይሆናል ፡፡
የውሃ ገንዳው የውሃ ውስጥ ሮቦቶችን ጥናት ለማካሄድ እና ጠፈርተኞችን ለማሰልጠን ሊያገለግል ይችላል የሚል እምነት ተፈጥሯል፡፡
እቅዶቹን የሚደግፉት የጠፈር ተመራማሪው ቲም ፒክ "ፕሮጀክቱ እንደጎዮሂሊ ኤርዝ ስቴሽን እና ስፔስፓርት ኮርንዌልን ያሉ ከፍተኛ ብሔራዊ ሃብቶች ይቀላቀላል። የሰው ልጆችን እና የፕላኔቶችን በሚጠቅም መልኩ እጅግ ከባድ በሆኑ አካባቢዎች ሰዎች እና ቴክኖሎጂዎች እንዴት እንደሚሠሩ ያለንን ዕውቀት ለማስፋት ይረዳል" ብለዋል፡፡
ለዕቅዱ ማስፈፀሚያ ፈቃድ ለማግኘት ማመልክቻ ያስገባው ብሉ አቢይስ የተባለው ኩባን ያለፕሮጀክቱ 10 ሄክታር ቦታ ይኖረዋል፡፡
ገንዳው 40 ሜትር በ 50 ሜትር ነው። 17 የኦሎምፒክ መጠን ያላቸውን የመዋኛ ገንዳዎች ለመሙላት የሚበቃ ውሃ ይይዛል። ተንሸራታች ጣሪያ የሚገጠምለት ሲሆን ትልልቅ ዕቃዎችን ወደ ገንዳው ለማስገባት የሚያስችል መጫኛና ማውረጃም ይኖረዋል።
የዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የሚመስሉ ክፍሎችን፣ የውሃ ውስጥ ፊልም ስብስቦችን እና በርቀት መቆጣጠሪያ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ለመፈተሽ እና ጥልቅ ዋናተኞችን ለማሰልጠን የሚያግዝ ዋሻ ይኖረዋል።
ፕሮጀክቱ የብሉ አቢይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የቀድሞው የጠላቂ ዋና አስተማሪው ጆን ቪከርስ ፈጠራ ነው፡፡
ገንዳው "በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ" እንደሚሆን እና "ሰፊ" ጥቅሞች እንደሚኖሩት ተናግረዋል፡፡
"ብሉ አቢይስ ለኤሮስፔስ፣ ለባህር ኃይል፣ ለዉሃ ሮቦት፣ ለሰው ልጅ ፊዚዮሎጂ፣ ለመከላከያ፣ ለመዝናናት እና ለባህር ኢንዱስትሪዎች ትልቅ የምርምር እንዲሁም ለህፃናት እና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድንቅ የትምህርት ማዕከል ይሆናል" ብለዋል፡፡
ቫይከር ለቅድመ-ግንባታ ወጪ የሚያስልገውን 5 ሚሊዮን ፓውንድ ያገኙ ሲሆን በ 18 ወራት ለሚጠናቀቀው ፕሮጀክት ግንባታ የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎች ተዘርግተዋል፡
ኩባንያው ለ 160 ሰዎች የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር እና ለአከባቢው ኢኮኖሚ በዓመት 8 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያስገኝ ገምቷል፡፡
የፓርላማ አባል የሆኑት ስቲቭ ደብል ፕሮጀክቱ ኒውኳይን በመምረጡ "እጅግ ደስ ብሎኛል" ብለዋል፡፡
"በርካታ አዳዲስ የኮርንዎል ታዳጊ ኢንዱስትሪዎች እንዲበለፅጉ የሚያደርግ፣ በሙያው የተካኑ ባለሙያዎችን የሚፈጥር እና በኢንዱስትሪዎች፣ በጥናትና ትምሀርት ዘርፎች ትብብር የሚፈጥር" ነው ብለዋል፡፡