በፖሊስ ሲፈለግ የነበረው ግለሰብ ሄሊኮፕተር ተከራይቶ እጁን ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኒው ዚላንድ የገጠር አካባቢ ተደብቆ በፖሊስ ሲታደን የነበረው ግለሰብ ወደ'ሚፈለግበት ፖሊስ ጣቢያ የሚያደርሰው ሄሊኮፕተር ተከራይቶ እጁን ሰጠ።
ጀምስ ብሪያንት በሰው ላይ በፈጸመው ጥቃት በተከፈተበት ክስ በኒው ዚላንዷ ትንሽ ከተማ ሰሜን ኦታጎ ውስጥ ከፖሊስ ተሰውሮ ለአምስት ሳምንታት መቆየቱ ተነግሯል።
እጁን ከሰጠ በኋላ ለአካባቢው መገናኛ ብዙሃን እንደተናገረው ተደብቆ የቆየበትን ጊዜ "ባጣም ጥሩ" እንደነበር ተናግሮ፤ ነገር ግን "ምንም ነገር ከሌለበት ስፍራ" ለመውጣት ዝግጁ ስለነበረ ፈልገው ሊያገኙት ወዳልቻሉት ፖሊሶች በፈቃዱ መምጣቱን ገልጿል።
ተፈላጊው ብርያንት በሰላም እጁን እንዲሰጥ ያግባባው የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተለው አርተር ቴይለር እንዳለው፤ ግለሰቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመግባቱ በፊት የምግብና የመጠጥ ግብዣ አድርጎለታል።
በገዛ ፈቃዱ እጁን የሰጠው ተፈላጊው ብርያንት የቀረቡበት ክሶች በጦር መሳሪያ ጥቃት መፈጸም፣ ሆን ብሎ ጉዳት ማድረስና ጎጂ የዲጂታል መልዕክቶችን ማስተላለፍን ይጨምራል።
ፖሊስ ብርያንን ለመያዝ እያፈላለገው በነበረበት ጊዜ ለነዋሪዎች ባስተላለፈው ማስጠንቀቂያ ግለሰቡ አደገኛና ማንም እንዳይቀርበው ብሎ ነበር።
ተጠርጣሪው ለአካባቢው ጋዜጣ እንደተናገረው ከፖሊስ ተሰውሮ በቆየበት ጊዜ ጊዜውን ዮጋ በመስራት ያሳልፍ እንደነበር አመልክቶ፤ በመጨረሻም ለኅብረተሰቡ ደኅንነት አደገኛ መባሉ ስላሳሰበው እጁን ለመስጠት መወሰኑን ገልጿል።
በዚህም ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሚያደርሰው ሄሊኮፕተር በገዛ ገንዘቡ ተከራይቶ "ለየት ባለ ሁኔታ" ለፖሊስ እጁን በመስጠት ታሪክ እንደሰራ ተነግሯል።
ተፈላጊው በተከራየው ሄሊኮፕተር ከተደበቀበት ወጥቶ ያለምንም ግርግር ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት እጁን በመስጠት ለሳምንታት ሲፈልጉት የነበሩ ፖሊሶችን አሳርፏቸዋል።












