ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዚነዲን ዚዳን ከሪያል ማድሪድ አሰልጣኝነት ለሁለተኛ ጊዜ ለቀቀ
የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ከቡድኑ አሰልጣኝነት ለሁለተኛ ጊዜ መልቀቁ ተነገረ።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያልተሳካለት ሪያል ማድሪድ የዚዳንን ከቡድኑ መልቀቅ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የአሰልጣኙን ውሳኔ "አሁን ማክበር አለብን" ብሏል።
ቡድኑ የ48 ዓመቱን አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ለዓመታት በነበረው ቆይታው ለሪያል ማድሪድ ላበረከተው "የሙያ ብቃትና ከፍተኛ ፍቅር" ምስጋና አቅርቧል።
የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዚዳን እአአ ከ2001 አስከ 2006 ለሪያል ማድሪድ የተጫወተ ሲሆን፤ በአሰልጣኝነት ቡድኑን በመራባቸው ከ2016 አስከ 2018 ባሉት ዓመታት ውስጥ በተከታታይ ሦስት የቻይምፒየንስ ሊግና የላ ሊጋ ዋንጫዎችን ማስገኘት ችሏል።
ቀደም ሲል ቡድኑን ከለቀቀ ከ10 ወራት በኋላ ተመልሶ ኃላፊነቱን በመረከብ ለሁለተኛ ጊዜ የላ ሊጋን ዋንጫ ለማንሳት አስችሏል።
"ዚዳን ከሪያል ማድሪድ ታላላቅ ከዋክብት መካከል አንዱ ሲሆን በቡድኑ ላይ በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት ያሳረፈው አሻራ ለዘመናት አብሮን ይኖራል" ሲል የቡድኑ መግለጫ ዚዳንን አሞግሶታል።
"እሱም በሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ቦታ እንዳለው ያውቃል፤ ቡድኑ ምንጊዜም ቤቱ ነው" ብሏል።
ቀጣይ የዚነዲን ዚዳን መድረሻ የት እንደሚሆን ለወራት የስፔን ጋዜጦች መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል።
ዚዳን በሪያል ማድሪድ ውስጥ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ሦስት ጊዜ በማንሳት ብቸኛው አስልጣኝ ሆኗል። በተጨማሪም ሁለት የዓለም ክለቦች ዋንጫን፣ ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ አሸናፊ እንዲሁም ሁለት የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫን በማሸነፍ ታሪክ ሰርቷል።