አንጀሊና ጆሊና ብራድ ፒት በጋራ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ተወሰነ

ታትሟል

ከረዥም ጊዜ እልህ አስጨራሽ የፍርድ ክርክር በኋላ ብራድ ፒት ከአንጀሊና ጆሊ ጋር ልጆቻቸውን በጋራ እንዲያሳድጉ ተወስኖለታል።

ታዋቂዋ አሜሪካዊት ተዋናይት ፍቺ የጠየቀችው በአውሮፓውያኑ 2016 ሲሆን ከዚያም በኋላ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ይዞት ነበር።

አሁን ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ብራድ ፒት ከልጆቹ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ በበለጠ ይጨምረዋል ተብሏል።

ታዋቂዎቹ የሆሊውድ ተዋናዮች በማደጎ ከኢትዮጵያ የወሰዷትን የ17 አመቷን ዘሃራን ጨምሮ፣ ፓክስ፣ ሺሎህና ቪቪየንና ኖክስ የተባሉ መንትዮች ወላጆች ናቸው።

የ19 አመቱ ማዶክስ እድሜው 19 በመሆኑ ከዚህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አልተካተተም።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም አንጀሊና ጆሊ ህጋዊ ትግሏን እንደምትቀጥል ፔጅ ሲክስ የተባለ ድረ-ገፅ አንድ ምንጭ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

አንጀሊና ጆሊ የተቃወመችው በአጠቃላይ በጋራ የማሳደጉን ሁኔታ ሳይሆን ሌሎች ስጋቶች እንዳሉባት ተገልጿል።

ለወራት ያህልም ፍርድ ቤቱ የተለያዩ የዐይን እማኞችን፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላትን ምስክርነት ሰምቷል።

አንጀሊና ጆሊ ልጆቻቸው ምስክርነት እንዳይሰጡ ተከልክለዋል በማለት የዳኛውን ውሳኔ ተቃውማለች።

ተዋናይቷ ለፍቺ ባስገባችው ጥያቄ ላይ ጥንዶቹ "የማይታረቅ ልዩነት እንዳላቸው" ገልፃ ነበር።

ብራድ ፒት በተወሰኑ ልጆቹ ላይ ያልተገባ ቁጣን ማሳየቱን ተከትሎ ጥቃት ያደርስባቸው ይሆን በሚል ምርመራ ቢደረግበትም በኋላ ነፃ ተብሏል።

ባለትዳሮቹ በብዙዎች ዘንድ የምርጥ ጥንድነት ምሳሌ ተደርገው ስማቸውን በማጣመር "ብራንጀሊና" የሚል ስያሜ በአድናቂዎቻቸው ተሰጥቷቸው ነበር።

ጥንዶቹ የተገናኙት ሁለቱም የተወኑበትና በአውሮፓውያኑ 2005 በተሰራው 'ሚስተር ኤንድ ሚስስ ስሚዝ' ፊልም ቀረፃ ላይ ነው።