በምዕራብ ጉጂ ዞን የጸጥታ ኃላፊን ጨምሮ 7 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት አንድ የአካባቢው ባለሥልጣንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
በምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በዞኑ የሚገኘው ገላና ወረዳ የጸጥታና የደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ጃርሶ በካሎን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን የወረዳው የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገበየሁ ያደቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ገበየሁ እንዳሉት ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 14/2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።
ከደቡብ ክልል የአማሮ ወረዳ ጋር በሚዋሰነው በዚህ አካባቢ እንዲህ ያለው ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ በፊትም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግድያዎች መፈጸማቸው ይታወሳል።
ባለፈው መጋቢት ወር ሁለቱ ወረዳዎች በሚያዋሰኑበት ሥፍራ ስብሰባ ላይ በነበሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ስድስት ደግሞ ቆስለው ነበር።
በወቅቱ ጥቃቱን የፈጸሙት መንግሥት 'ሸኔ' ብሎ የሚጠራውና እራሳቸውን 'የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት' የሚሉት ታጣቂዎች እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፤ አሁንም ለሰባት ሰዎች ህልፈት ምክንያት ለሆነው ጥቃት ይኸው ታጣቂ ቡድን በተጠያቂነት ይከሰሳል።
በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ በሰዎች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶችና የንብረት ውድመቶች ጋር በተያያዘ ከሳምንታት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡድኑን ሽብርተኛ ቡድን ብሎ መሰየሙ ይታወሳል።
ከሳምንት በፊት የቀድሞ የምዕራብ ወለጋ ዞን ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ አምስት የመንግሥት ሠራተኞች በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀው ነበር።
የምዕራብ ጉጂው ጥቃት
በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገበየሁ ያደቴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃቱ በታጣቂዎቹ የተፈጸመው ኃላፊውና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለሥራ እየተጓዙ በነበረበት ጊዜ ነው።
"በዚህም በወረዳው የጸጥታና የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጃርሶ በካሎ የተመራ ቡድን የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቦሬ ቀበሌ እየተጓዘ ሳላ ጨልቤሳ ሾሮ በተባለ ሥፍራ ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው" ብለዋል።
በጥቃቱም ከወረዳው አስተዳደር ወገን የነበሩ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ከታጣቂዎቹ በኩል ደግሞ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
በጥቃቱ ሁለት የሚሊሻ አባላት፣ ሦስት የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት፣ የወረዳው ጸጥታና ደኅንነት ኃላፊና እና የጽህፈት ቤቱ የደኅንነት ባለሙያ በአጠቃላይ 7 ሰዎች ተገድለዋል።
በታጣቂዎቹ ከተገደሉት ባሻገር ሌሎች 7 ሰዎች ደግሞ በተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ዲላ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን አቶ ገበየሁ ገልጸዋል።
በጥቃቱ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ሰባት ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በጥቃቱ ወቅት ከታጣቂዎቹ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሁለት የታጣቂው አባላት መሞታቸው ተነግሯል።
በአካባቢው የአመራር አባላትና የጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሥፍራ የተጠናከረ አሰሳና እርምጃ እየተወሰደ መሆኑም ኃላፊው ገልጸዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት የምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ታጣቂዎች ድንበር ላይ ባሉ የወረዳው ቀበሌዎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱና በተለያዩ ጊዜያትም በጸጥታና በሚሊሻ አባላት ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ጨምረው አመልክተዋል።
ቅዳሜ ዕለት በታጣቂዎቹ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ሥርዓተ ቀብር እሁድ ዕለት መፈጸሙንም የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መረጃ በዚህ ዓመት ብቻ በኦሮሚያ ክልል 'ሸኔ' በተባለው ታጣቂ ቡድን በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ18 በላይ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ 112 የፖሊስ አባላት እንዲሁም 57 በሚሊሻ አባላት በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ ውስጥ ተገድለዋል።














