በአሜሪካ ትልቁ የነዳጅ ማስተላለፊያ ድርጅት ለወንጀለኛ ቡድን 4.4 ሚሊየን ዶላር መክፈሉን አመነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው የነዳጅ ማስተላለፊያ ድርጅት ለመረጃ ጠላፊ ቡድን 4.4 ሚሊየን ዶላር የድርድር ገንዘብ መክፈሉን አረጋጋጠ።
በአሜሪካ ትልቁ የነዳጅ ማስተላለፊያ ድርጅት -ኮሎኒያል ፓይፕላይን የአሜሪካን የነዳጅ ማስተላለፊያ ሥርዓት በመዝጋት ተጠያቂ ነው ለተባለ መረጃ ጠላፊ ቡድን ነው 4.4 ሚሊየን ዶላር የድርድር ገንዘቡን የከፈለው።
የድርጅቱ ኃላፊ ወንበዴዎቹ የነዳጅ ማስተላለፊያ ሥርዓቱን ለምን ያህል ጊዜ ዘግተውት እንደሚቆዩ ማወቅ ባለመቻሉ እአአ ግንቦት 7 ክፍያው እንዲፈፀም መፍቀዳቸውን ለዎል ስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።
የድርጅቱ ኃላፊ ጆሴፍ ብላንት የመረጃው ጠለፋ ከተካሄደ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ቃለ ምልልስ "በጣም አነጋጋሪ ውሳኔ እንደሆነ አውቃለሁ" ብለዋል።
8 ሺህ 900 ኪሎ ሜትር (5ሺህ 500 ማይልስ) የሚረዝመው የነዳጅ ማስተላላፊያ ቱቦ በቀን 2.5 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ያስተላልፋል።
እንደ ድርጅቱ ከሆነ ማስተላለፊያ ቱቦው 45 በመቶ የሚሆነውን የምስራቅ ባህር ዳርቻዎች የናፍጣ፣ ፔትሮሊየምና የጀት ነዳጅ ፍጆታን ይሸፍናል።
ዋና ኃላፊው ብላንት ለጋዜጣው እንደተናገሩት ድርጅቱ የመደራደሪያ ገንዘቡን ለመክፈል የወሰነው ከጥቃቱ ጀርባ ካለው 'ዳርክሳይድ' የወንጀል ድርጅት ጋር ቀደም ብሎ ከተነጋገሩ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው።
"እኔ ውሳኔውን በቀላሉ አልወሰንኩም። ለእነዚህ ዓይነት ሰዎች ገንዘብ ሲወጣ ደስ አላለኝም ነበር። ነገር ግን ለአገሪቷ ሲባል የተደረገ ትክክለኛ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ወደ ፊት መሰል ድርጊቶችን ያበረታታል በሚል ድርጅቶች ከወንጀለኞች በሚደርሳቸው ማስፈራሪያ የድርድር ገንዘብ እንዳይከፍሉ ሃሳብ ሰጥቶ ነበር።
ኮሎኒያል ፓይፕላይን የሳይበር ጥቃት ካጋጠመው በኋላ እአአ ግንቦት 7 ተዘግቶ ነበር ።
እንደ ጋዜጣው ከሆነ በቢትኮይኑ ለተከፈለው ክፍያ ምላሽ ድርጅቱ በጠላፊዎቹ ተዘግቶ የነበረውን ሥርዓቱን እንደገና የሚከፍትበትን ዘዴ የተቀበለ ቢሆንም ይህ ግን ሥርዓቱን ወዲያውኑ ለማስጀመር በቂ አይደለም።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው ሥራውን ባለፈው ሳምንት ጀምሯል። ይሁን እንጅ የፔትሮሊየም እጥረት በሰሜን ካሮላይና እና ጆርጅያ አጋጥሟል።
የድርጅቱ ኃላፊ ብላውት እንዳሉት ሌሎች የንግድ ተቋማት እስከሚያገግሙ ድረስ እጥረቱ ለወራት ሊዘልቅ ይችላል ብለዋል። የሳይበር ጥቃቱም ድርጅቱን አስር ሚሊየን ዶላሮች እንደሚያስወጣው ገምተዋል።
በሳይበር ጥቃቱ ወቅት 'ዳርክሳይድ' የተባለው የወንጀለኛ ቡድን ድርጊቱን መፈፀሙን በይፋዊ መግለጫው አስታውቆ ነበር።
ቡድኑ "ዓላማችን ገንዘብ መስራት እንጅ ማሕበረሰቡ ላይ ችግር መፍጠር አይደለም" ሲሉም በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።












