በኢትዮጵያ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተቋርጠው እንደነበር ተነገረ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የኢንተርኔት ነጻነትን የሚከታተከለው ኔትብሎክስ ኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበራዊ ሚዲያ መገልገያ መተግበሪያዎች አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር አስታወቀ።

ኔትብሎክስ እንዳለው ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ፌስቡክን ጨምሮ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ያለው መረጃ እንደሚያመለክት ገልጿል።

ከአዲስ አበባ የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳረጋገጠው ፌስቡክ ለመጠቀም አስቸጋሪ እንደሆነ ነገር ግን ቪፒኤን በተባለው ተዘዋዋሪ የመጠቀሚያ መተግበሪያ አማካይነት መግባት እንዳስፈለገው አመልክቶ፤ ዋትስአፕን ለመጠቀም ምንም ችግር እንዳልገጠመው ገልጿል።

ቢቢሲ ከአዲስ አበባ ውጭ ያለውን እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ መገልገያዎች መቋረጥ በተመለከተ ከአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች ለማጣራት ባደረገው ሙከራ ችግሩ በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በድሬዳዋና በሐዋሳ ማጋጠሙን አመልክተዋል።

ነገር ግን አገልግሎቶቹ ለሰዓታት ተቋርጠው ከቆዩ በኋላ ሰኞ ረፋድ ከአራት ሰዓት በኋላ መመለሱን ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል።

ቢቢሲ የተጠቀሱት የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ከአገልግሎት ውጪ መሆንን በተመለከተ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ከአንድ የኢትዮቴሌኮም ኃላፊ እንደተረዳው ክስተቱ ከተቋማቸው ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ያጋጠመ መሆኑን ተናግረዋል።

የፌስቡክና የኢንስታግራም መተግበሪያዎቹ አገልግሎት ያቋረጠው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በመላው አገሪቱ ውስጥ እንደነበር ኃላፊው ገልጸዋል።

እነዚህ ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ለሰዓታት የቆዩት የማኅበራዊ ሚዲያ መገልገያዎች ከጠዋቱ አራት ሰዓት በኋላ መስራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ አለመረጋጋቶችን እንዲሁም ብሔራዊ ፈተናዎችን ተከትሎ የኢንተርኔትና የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶች በተደጋጋሚ መዘጋታቸው ይታወሳል።