በሩሲያ ትምህርት ቤት በተከፈተ ተኩስ ተማሪዎች እና መምህር ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሩሲያ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት በተከፈተ ተኩስ ተማሪዎች እና መምህራን ተገደሉ።
በጥቃቱ የተገደሉ ተማሪዎች አሃዝን በተመለከተ የተለያዩ ዘገባዎች ቢወጡም የአከባቢው ባለስልጣናት ግን ቢያንስ 7 ታዳጊ ተማሪዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
ከሟቾቹ በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጆች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ፖሊስ ከሩሲያ መዲና 820 ኪ.ሜትር ርቃ በምትገኘው ታታርስታን ግዛት በደረሰው ጥቃት የተጠረጠረ አንድ ወጣት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
የግዛቷ ፕሬዝደንት ጥቃቱን 'አሳዛኝ’ ያሉት ሲሆን፤ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው የአገሪቱን የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ሕግን እንደሚያጠብቁ ተናግረዋል።
ስለ ጥቃቱ እስካሁን የምናውቀው
በትምህርት ቤቱ ላይ ተኩስ እንደተከፈተ ፖሊስ እና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በትምህርት ቤት አቅራቢያ በፍጥነት ነበር የደረሱት።
በማሕበራዊ ሚዲያ በስፋት የተጋሩ ምስሎች ላይ ተማሪዎች እራሳቸውን ለማዳን በመስኮት ሲዘሉ ታይተዋል።
አንድ የሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሕይወታቸው ያለፈው ከሁለተኛ ፎቅ ላይ በመስኮት በኩል ከዘለሉ በኋላ ነው ሲል ዘግቧል።
የግዛቷ አስተዳዳሪ 4 ወንድ እና 3 ሴት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው ብለዋል።
አንድ መምህርም መገደሉን የግዛቷ አስተዳዳሪ ጽ/ቤት አስታውቋል። ከሟቾች በተጨማሪ 6 ተማሪዎች ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
የአከባቢው ባለስልጣናት ጥቃቱን ያደረሰው አንድ ግለሰብ ብቻ ነው ብለዋል። “አንድ የ19 ዓመት አሸባሪ በቁጥጥር ሥር ውሏል። የጦር መሳሪያ መሸጫ መደብር ባለቤት ነው” ሲሉ የግዛቷ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
ጥቃቱ እንደተሰማ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የአገሪቱ ደህንነት ተቋም በሕብረተሰቡ ውስጥ ተሰራጭቶ ስለሚገኘው የጦር መሳሪያ አይነት ዝርዝር መረጃ እንዲያቀርቡላቸው ማዘዛቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ፖሊስ ጥቃት ሳያደርስ አይቀርም የተባለው ግለሰብ የሚኖርበት አከባቢ የቤት ለቤት ፍተሻ እያደረገ ስለመሆኑ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።












