የካታር የገንዘብ ሚኒስትር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY
የካታሩ የገንዘብ ሚኒስትር ስልጣናቸውን ከልክ በላይ በመጠቀምና የህዝብን ሀብት በመመዝበር ወንጀል ተጠርጥረውበቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
“ከሲቪል ሰርቪስ ጋር በተያያዙ ወንጀል” ‘ግምገማ’ ከተደረገባቸው በኃላ የካታሩ የገንዘብ ሚኒስትር አሊ ሸሪፍ አልኤማዲ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ነው የካታር ዜና አገልግሎት የዘገበው።
በጉዳዩ ላይ ግን ተጠርጣሪው ሚኒስትር አሊ ሻሪፍ አልኢማዲ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ሚኒስትሩ፤ የካታርን 300 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሉአላዊ ሃብት የሚቆጣጠረው ቦርድ የበላይ ጠባቂና የብሄራዊ ባንክ ሊቀመንበር ነበሩ።
ሰውዬው የካታር ገንዘብ ሚኒስትር ሆነው በ2013 ከመሾማቸው በፊት ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ትልቁ አበዳሪ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ነበሩ።
እንዲህ ስማቸው በክፉ ከመነሳቱ በፊት እኚሁ ሚኒስትር ብሪቴይን ውስጥ የሚታተም ‘ዘ ባንከር’ የተባለ መጽሄት ባለፈው ዓመት በመካከለኛው ምስራቅ ‘የአመቱ ምርጥ ሚኒስትር’ ብሏቸው ነበር።
መጽሄቱ በኮሮናቫይረስ ወቅት የካታርን ኢኮኖሚ በተሻለ ሁኔታ መርተውታል ሲል አሞካሽቷቸዋል።
አሁን በተጠረጠሩበት ወንጀል ዙሪያ የካታር ዜና አገልግሎት ዝርዝር መረጃን አላቀረበም።
‘ዘ ፋይናንሻል ታይምስ’ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያለውን ምንጭ ጠቅሶ ሚኒስትሩ “ጉቦና በመንግስት ኮንትራቶች” ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ዘግቧል።
በካታር እንዲህ አይነት እስር የተለመደ አይደለም። ሆኖም ቀጣዩን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ እየተሳናዳች ያለችው ሃገር የሙስና ቀዳዳዎቿን ለመድፈን እየሰራች ነው።
ይህንን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ካታር ለስቴዲየምና ለመሰረተ ልማት ግንባታ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሳለች።
ካታር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙስናን በመከላከል ከ180 ሀገራት በ30ኛ ደረጃ ተቀምጣለች። ከአረብ ሀገራት ደገሞ ከዩኤኢ በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር ናት።














