ኢራን የኒውክሌር ጣቢያዋ ላይ ጥቃት ፈፅሟል ያለችውን ግለሰብ ማንነት አስታወቀች

ሬዛ ካሪሚ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በቅርቡ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያ ላይ የደረሰውን ጥቃት ፈፅሟል የተባለውን ግለሰብ ማንነት የአገሪቱ ቴሌቪዥን አስታውቋል።

ቴሌቪዥን ጣቢያው በናታንዝ ኒውክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት በመፈፀም ወንጀል እጁ አለበት የተባለውን ግለሰብ የደህንንት ባለስልጣናቶችን ዋቢ አድርጎ ነው የዘገበው።

ሬዛ ካሪሚ የተባለው ግለሰብ ፍንዳታው ከደረሰ በኋላ በፍጥነት ኢራንን ለቆ መውጣቱን ኔትወርክ ዋን ዘግቧል። በአለም አቀፉ ወንጀል አዳኝ ኢንተርፖል የተለቀቀውን ፎቶም አሳይቷል።

ኢንተርፖል በበኩሉ ሬዛ ካሪሚ በቀይ መዝገቡ ካሰፈራቸው ተፈላጊ ወንጀለኞች ዝርዝር ውስጥ አንዱ መሆኑን አላረጋገጥኩም ብሏል።

ጥቃቱ እንዴት እንደተፈፀመ ዝርዝር መረጃዎች ባይኖሩም የኢራን ፓርላማ ምርምር ማዕከል ኃላፊ አሊሬዛ ዛካኒ እንዳሉት የኒውክሌር ቁሶችን ለማብላላትና ለማጣራት የሚያገለግሉ ማሽኖች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።

ጥቃቱ ከመሬት በታች 50 ሜትር በሚገኝ ተቋም እንደሆነ አንድ ባለስልጣን ተናግረዋል።

በባለፈው ሳምንት ለደረሰው የኒውክሌር ጥቃት ኢራን እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች። የኒውክሌር ተቋሟቷንም ደህንንት ለመጠበቅ አጥብቃ እየሰራችም እንደሆነ አስታውቃለች።

አስራኤል በበኩሏ ይፋዊ በሆነ መልኩ ጥቃቱን ማድረስ አለማድረሷን ያለችው ነገር የለም። ነገር ግን የእስራኤል ሬድዮ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ በሞሳድ እንደተፈፀመ ዘግቧል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ኢራን የ2015 የኒውክሌር ስምምነትን አሰመልክቶ ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያና ጀርመን ጋር እንደገና ውይይት ለማድረግ እያቀደች ባለችበት ወቅት ነው።

ስምምነቱ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሳሪያ እንዳይኖራት የሚያግድ ሲሆን ኢራን በበኩሏ ኒውክሌርን በጦር መሳሪያነት የመጠቀም እቅዱ የለኝም ትላለች።

ለእስራኤል ይህ ስምምነት ተቀባይነት የለውም፤ ኢራንን የኒውክሌር ኃይል እንዲኖራት ከማድረግ አያግዳትም ትላለች።

በስምምነቱ መሰረት ኢራን የኒውክሌር ተቋማት እንቅስቃሴዎችን የምትገድብ ከሆነ የተጣለባት ማዕቀቦችም ይላል የሚል ነበር። ነገር ግን ስምምነቱን በአውሮፓውያኑ 2018 ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም ጥለው ከወጡ በኋላ አደጋ ላይ ነው ተብሏል።

ከባለፈው ጥቃት በኋላ ኢራን የምታበለፅገውን ዩራኒየም ወደ 60 በመቶ መጠን እንደሚኖረው ውሳኔ ላይ የደረሰች ሲሆን ይህም ስምምነቱን የሚጥስ ነው ተብሏል።