ቤይጂንግ የዓለማችን በርካታ ቢሊየነሮች የሚገኙባት ከተማ ተባለች

ቤይጂንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቻይናዋ ዋና ከተማ ቤይጂንግ በአሁኑ ጊዜ ከየትኞቹም የዓለማችን ከተሞች በበለጠ የበርካታ ቢሊየነሮች መኖሪያ መሆኗን ፎርብስ ያወጣው የባለጸጎች ዝርዝር አመለከተ።

ቤይጂንግ ቀደም ሲል ከነበሯት ቢሊየነሮች ቁጥር ላይ ባለፈው ዓመት 33 ባለጸጎችን ጨምራለች።

ከተማዋ ካሏት ነዋሪዎች መካከል አንድ መቶዎቹ የናጠጡ ሀብታሞች እንደሆኑ ፎርብስ መጽሔት አመልክቷል።

በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት በባለጸጎች ብዛት የቀዳሚነቱን ቦታ ይዛ የነበረችውን የአሜሪካዋን ኒው ዮርክ በልጣታለች። በኒው ዮርክ 99 ቢሊየነሮችን ይኖራሉ ተብሏል።

በዚህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ቻይና በሽታውን በፍጥነት መቆጣጠር መቻሏ፣ እያደጉ በመጡ የቴክኖሎጂ ተቋማትና የአክስዮን ገበያዎች ምክንያት ቀዳሚውን ቦታ ለመያዝ ችላለች።

ቤይጂንግ ምንም እንኳን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ያላቸው ባለጸጎችን በውስጧ ብትይዝም፤ የሁሉም የሀብት መጠን በአንድ ላይ ሲደመር ግን የኒው ዮርክ ባለጸጎችን ሊበልጥ አልቻለም።

የኒውዮርክ ቱጃሮች ገንዘብ በአጠቃላይ ሲደመር 58 ቢሊየን ዶላር በመሆን የቻይናዎቹን ይበልጣል።

በቤይጂንግ ካሉ ሃብታም ግለሰቦች መካከል፣ የቪዲዮ ማጋሪያ መድረክ የቲክቶክ ባለቤት የሆነው፣ ዣንግ ይሚንግ ሲሆን የተጣራ የሀብቱ መጠን 35.6 ቢሊየን ዶላር ነው።

በንጽጽር የኒው ዮርክ ከተማ ባለጸጋ የሆነው የቀድሞው የከተማው ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ የሀብቱ መጠን ደግሞ 59 ቢሊየን ዶላር ነው።

በኮሮናቫይረስ ዘመን በርካታ ሰዎች በኢንተርኔት አማካይት የሚገበያዩበትና የመዝናኛ ዘዴዎችን በመጠቀማቸው በቻይና በአሜሪካ ያሉ የቴክኖሎጂ ተቋማት ከፍተኛ እድገትን አስመዝግበዋል።

ይህም ለግዙፎቹ ተቋማት መስራቾችና የድርሻ ባለቤቶች ሀብት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን አስገኝቶላቸዋል።

ፎርብስ መጽሔት ላዘጋጀው ዝርዝር ሆንግ ኮንግንና ማካዎን ከቻይና ጋር በአንድነት ያቀረበ ሲሆን በዚህም አገሪቱ ከየትኛውም የዓለም አገር በበለጠ 210 አዳዲስ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ለመሆን ችላለች።

ከቻይና ቢሊየነሮች ውስጥ ግማሽ ያህሎቹ ሀብታቸውን ያገኙት ከምርትና ከቴክኖሎጂ ዘርፎች ሲሆን፤ ይህም ኬት ዋንግ የተባለችውን በኢ-ሲጋሬት (ዘመናዊ ሲጋራ) ምርት ቢሊየነር የሆነችውን ሴት ያካትታል።

ቻይና በአጠቃላይ 698 ቢሊየነሮች ሲኖሯት፣ በ724 ቢሊየነሮች ቀዳሚ ወደ ሆነችው አሜሪካ ቀስ በቀስ እየተጠጋች ትገኛለች።

ፎርብስ እንደሚለው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 493 አዲስ ቢሊየነሮች ወደ ዝርዝሩ ውስጥ ተቀላቅለዋል፤ ይህም በየ17 ሰዓቱ አንድ ቢሊየነር ወደ ሀብት ማማው ላይ ወጥቷል ማለት ነው።

ከአሜሪካና ቻይና በመከተል ሦስተኛዋ የቢሊየነሮች አገር የሆነችው ሕንድ ናት፤ 140 ቢሊየነሮች አሏት።

በእስያ ፓሲፊክ አካባቢ አገራት ውስጥ ያሉ የ1,149 ቢሊየነሮች አጠቃላይ ሀብታቸው 4.7 ትሪሊየን ዶላር ሲሆን በአሜሪካ ያሉ ቢሊየነሮች ሀብት ደግሞ 4.4 ትሪሊየን ዶላር ነው።

የአማዞን መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው አሜሪካዊው ጄፍ ቤዞስ አሁንም የምድራችን ቀዳሚው ባለጸጋ በመሆን ለአራት ተከታታይ ዓመታት እየመራ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የቤዞስ የሀብት መጠን በ64 ቢሊየን ዶላር አሻቅቦ 177 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።