ሱዳን ውስጥ 'መንግሥታዊ ሐይማኖት' እንዳይኖር ስምምነት ተፈረመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአገሪቱ በመንግሥት የሚደገፍ ሐይማኖት እንዳይኖር የሚያደርግ መንግሥትና ሐይማኖትን የሚለይ ስምምነትን ሱዳን ፈረመች።
የሱዳን መንግሥት በአገሪቱ ካሉ አመጺ ቡድኖች ጋር በሚያደርገው ንግግር ቀጥሎ ነው እዚህ ስምምነት ላይ የደረሰው።
ትናንት እሁድ ዋንኛ አማጺ ከሚባለውና በደቡባዊ የኑባ ተራሮች መሽጎ ከሚገኘው አማጺ ቡድን ጋር አዲስ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።
የዚህ ስምምነት ዋንኛው አምድ መንግሥትና ሐይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ አንቀጽ ነው ተብሏል። ስምምነቱ የሐይማኖትና የባሕል ብዝሃነትን የሚቀበል እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ስምምነት አብዱልፈታህ አልቡርሐን የሚመሩት የሱዳን ጥምር መንግሥት አመጺ ኃይሎችን ወደ ጠረጴዛ ውይይት ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል ተደርጎ ተወስዷል።
ሱዳን የቀድሞውን የአልበሽርን አስተዳደር የተቃወሙ በርካታ አማጺያን ነፍጥ አንስተው በሚሊዮኖች ተፈናቅለው በመቶ ሺዎች የሞቱባት አገር ናት።
ባለፈው ዓመት አዲሱ የአልሐርሃንና የአብደላ ሐምዶክ ጥምር የወታደራዊና ሲቪል አስተዳደር ከምዕራብ ሱዳኑ ክልል የዳርፉር አመጺ ጋር የተሳካ የተባለ ስምምነት ማድረጉ አይዘነጋም።
ሆኖም ባለፈው ዓመት ከበርካታ አመጺዎች ጋር ስምምነት ሲደረግ የሱዳን ሕዝቦች የነጻነት ንቅናቄ በምህጻሩ ኤስፒኤልም-ኤን ጋር ከስምምነት መደረስ ሳይችል ቀርቶ ነበር።
በአብዱልአዚዝ አል-ሂሉ የሚመራው ይህ አማጺ ቡድን ስምምነቱን ያልተቀላቀለው ሱዳን በሸሪአ የምትተዳደር አገር መሆኗን በመቃወም ነበር።
ሐይማኖታዊ መንግሥትን የሚቃወመው የአብዱልአዚዙ አማጺ ቡድን ትናንት ከሱዳን ጥምር ጊዜያዊ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት ሱዳን ኢስላማዊ መንግሥትነትን ለመተው በመፍቀዷ ነው ፊርማውን ያኖረው።
በሱዳን የሸሪዓ ሕግ ተግባራዊ የተደረገው እንደ አውሮፓዊያኑ በ1983 ነበር።
በሕዝባዊ አመጽ ሥልጣናቸውን ያጡት ኦማር አልበሽር በሱዳን ለ30 ዓመታት ያህል በመሪነት ቆይተዋል።
በዚህ ትናንት በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ሐይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸው ተገልጿል።
በመግባቢያ ስምምነቱ ሱዳን ነጻ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ የሐይማኖት እኩልነት የሰፈነባት አገር እንደምትሆን ተመላክቷል።
ኤስፒኤልኤም-ኤን የሚንቀሳቀስበት የሱዳን ክልል የክርስትና አማኞች የሚበዙበት ሲሆን በአልበሽር ዘመን በእምነታቸው ምክንያት ብዙ መከራን ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ነፍጥን ለማንገብ ተገደው ነበር።












