ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ ኪንግደም፡ በብሪስቶል ከተማ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች በፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት ፈፀሙ
በዩናይትድ ኪንግደም ብሪስቶል ከተማ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች በፖሊስ አባላት ጥቃት ሰንዝረው ንበረት አወደሙ።
ሰልፈኞቹ አዲስ የረቀቀው የፖሊስ እና የወንጀል ሕግን በመቃወም የጠሩት ሰልፍ እንዳይካሄድ እና ሰዎችም ሰልፍ እንዳይወጡ የአከባቢው ባለስልጣናት ጠይቀው ነበር።
ወደ ኃይል በተቀየረው የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ አባላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የፖሊስ መኪኖችም በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል።
ሰልፈኞቹ የሚቃወሙት አዲሱ ሕግ ሲጸድቅ የእንግሊዝ እና የዌልስ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማስቆም እና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ስልጣን ያገኛል።
ሰልፈኞቹም ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመቆጣጠር ያልተገባ ስልጣን ማግኘት የለበትም ይላሉ።
ሰልፈኞቹ ፖሊስ ጣቢያን ወረዋል፣ ርችቶችንም ወርውረዋል እንዲሁም በፖሊስ ንብረቶች ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን ጽፈዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስትሩ ፕሪቲ ፓቴል ድርጊቱን “ተቀባይነት የሌላው” ሲሉ ገልጸውታል።
“በአናሳዎች የሚፈጸም ስርዓት አልበኝነትን አንታገስም” ያሉ ሲሆን የፖሊስ አባላት ማህብረሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ እራሳቸውን ለጉዳት ማጋለጣቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ሰላማዊ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በጥቂት ግለሰቦች አማካይነት ወደ አመጽ ተቀይሯል ብሏል።
ፖሊስ ጨምሮም በንብረቶች እና በፖሊስ አባላት ላይ የደረሰውን ጉዳት ዘርዝሯል።
በሪፖርቱ መሠረት ቢያንስ ሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ደርሷል።
ፖሊስ በዚህ የአመፅ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ተለይተው ከሕግ ፊት ይቀርባሉ በሏል።
የተቃውሞ ስለፉን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ስለመኖራቸው ግን የተባለ ነገር የለም።
የብሪስቶል ከተማ ከንቲባ ማርቪን ሪስ “የተቃዋሚዎች ብስጭት እረዳለሁ ይሁን እንጂ በህንጻዎች እና መኪኖች ላይ ጉዳት ማድረስ እና በፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ሕጉ ከመጽደቅ ወደ ኋላ አያስቀርም” ብለዋል።
በከተማዋ መሰል አመጽ የተቀላቀለበት ሰልፍ ሲካሄድ ከበርካታ ዓመታት ወዲህ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።