የ96 አመቱ የቀድሞ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ጠባቂ ችሎት መቅረብ እንደሚሳናቸው ፍርድ ቤቱ ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በጀርመን የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት የቀድሞ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ግለሰብ የነበሩ የ96 አመት ግለሰብ በእድሜያቸውና አካላቸው መድከም ጋር ተያይዞ ችሎት መቅረብ እንደሚሳናቸው ውሳኔ አስተላልፏል።
ነገር ግን ከፍርድ ሂደቱ ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን ሊፈፅሙ ይገባል ብሏል።
ሃሪ ኤስ የተባሉት ግለሰብ ስተትሆፍ በተባለ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የደረሰ ጭፍጨፋ ላይ እጃቸው አለ በሚል ነበር ተከሰው የነበረው።
በማጎሪያ ካምፑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።
ፍርድ ቤቱ እንዳለው ግለሰቡ "በጭፍጨፋው እንደተሳተፈ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች" አሉ ብሏል።
በናዚ ጦር ተይዛ በነበረችው ፖላንድ ውስጥ ይገኝ ነበር በተባለው ስተትሆፍ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በደረሰ ጭፍጨፋ በቅርቡ ተከሰው ከነበሩት ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ብሩኖ ዴይ የተባሉት የ93 አመት ግለሰብ አምስት ሺህ ታራሚዎች ግድያ ላይ እጃቸው አለበት በሚል ተከሰው፤ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው የሁለት አመት እስር ፈርዶባቸዋል ።
ከዚህም በተጨማሪ በማጎሪያ ካምፑ በፀሃፊነት ያገለግሉ ነበር የተባሉት የ95 አመቷ ኢርምጋርድ ኤፍ ግድያና ጭፍጨፋ አስተባብረዋል በሚል ተከሰዋል።
በናዚ ወቅት በደረሱት ግድያዎች ከተከሰሱት ጥቂት ሴቶች መካከል አንደኛዋ ሆነዋል።
ሃሪ ኤስ በስተትሆፍ የማጎሪያ ካምፕ ከአውሮፓውያኑ 1944-1945 በጠባቂነት አገልግለዋል።
በዚህም ወቅት 600 የሚሆኑ ታራሚዎች ወደ ኦሽዊትዝ ቢርኬናው ማጎሪያ ካምፕ ተወስደው በመርዝ እንዲገደሉ ሲወሰን፤ ሃሪ ኤስ በጠባቂነት አጓጉዘዋቸዋል ተብሏል።
ግለሰቡ ግድያና ጭፍጨፋዎችን አስተባብረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው በአውሮፓውያኑ 2017 ነው።
ስተትሆፍ ካምፕም ቢሆን ይሁዲዎችን የሚያሰቃይበትና የሚገድልበት የመርዝ ማፈኛ ቦታ ነበረው ተብሏል።
በዚህ ማጎሪያ ካምፕ ከመቶ ሺህ በላይ ታራሚዎች ነበሩ። በርካቶቹ በረሃብ፣ በመርዛማ ጋዝ እንዲሁም በሽጉጥ ተተኩሶባቸው እንደተገደሉ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ምንም እንኳን በዚህ ቦታ ላይ የነበሩት በርካቶቹ ይሁዲዎች ቢሆኑም የፖላንድ ዜጎችና የተማረኩ የሶቪየት ወታደሮችም ነበሩበት ተብሏል።
የምዕራቡ ጀርመን ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ "ባለው የእድሜና አካሉ መድከም የተነሳ ሃሪ ኤስ ችሎት ላይ መቅረብ ይሳነዋል" በማለት ክሱን ውድቅ አድርጎታል።
ነገር ግን ይህም ማለት ከወንጀሉ ነፃ እንዳልሆኑና የተከሰሱባቸውን ጭፍጨፋዎችን አስተባብረውም እንደሆነ ፍርድ ቤቱ እንደሚያምን አስታውቋል።












