ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መዳብ ተብሎ ድንጋይ የተሸጠለት ድርጅት 36 ሚሊዮን ዶላር ተጭበረበረ
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 36 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት መዳብ ከቱርክ ኩባንያ የገዛው ድርጅት ቀለም የተቀባ ድንጋይ እንደደረሰው አስታወቀ።
አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ በ36 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት የገዛውን መዳብ፤ አቅራቢ ኩባንያው ቀለም በተቀቡ ድንጋዮች ቀይሮ እንዳስረከበው ገልጿል።
መቀመጫውን ጄኔቫ ያደረገው ሜርኩሪያ ኢነርጂ ግሩፕ 10,000 ቶን የመዳብ ግዢ መፈጸሙን ተከትሎ በጭነት ማጓጓዝ (ካርጎ) ወቅት ተጭበርብሬያለሁ ብሏል።
ጭነቶቹ ቻይና ሲደርሱ በመዳቡ ምትክ ቀለም በተቀቡ ድንጋዮች የተሞሉ ኮንቴይነሮችን ሆነው ተገኝተዋል።
የደኅንነት እና የፍተሻ ቁጥጥሮች ቢከናወኑም መጭበርበሩ መፈጸሙ ተነግሯል።
ባለፈው ዓመት ሜርኩሪያ መዳረሻው ቻይና እንዲሆን ያቀደውን መዳብ ለመግዛት ተስማምቶ ከ300 በላይ ኮንቴይነሮች ውስጥ 6,000 ቶን ያህል መዳብ በስምንት መርከቦች ተጭነውለታል።
ኢስታንቡል አቅራቢያ ከሚገኘው ወደብ ጭነቱ መጓጓዝ ከመጀመሩ በፊት፣ በከፊል የተጣራውን መዳብ በሚመስሉ ቀለም በተቀቡ የተጠረቡ ድንጋዮች ተቀይሯል።
በዓለም ላይ ካሉ አምስት ታላላቅ የነዳጅ ነጋዴዎች አንዱ የሆነው ሜርኩሪያ በመዳብ አቅራቢው በቢኤትሳን ባኪር ላይ በቱርክ እና በእንግሊዝ ፍርድ ቤቶች ፍትህ ለማግኘት እየጣረ ነው።
የቱርክ ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር የሚያያዙ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ኩባንያው በመግለጫው ላይ "በዚህ የተደራጀ ወንጀል ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል" ካለ በኋላ ኢስታንቡል የፋይናንስ ወንጀሎች መምሪያን አመስግኗል።
ቁልፎች ተሰብረዋል
በአጣሪ ኩባንያ ምርመራ ከመካሄዱ በፊት መዳቦቹ ወደ መጀመሪያዎቹ ኮንቴነሮች የተጫኑ ይመስላል። ማጭበርበርን ለመከላከል ጥቅም ላይ የዋሉ ማህተሞች በዕቃዎቹ ላይ ተደርገዋል።
ነገር ግን ኮንቴነሮቹ ተከፍተው መዳቦቹ በድንጋዮች ተተክተዋል ሲል የኢስታንቡል የሕግ ኩባንያ ኬዋይቢ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሯል። አጭበርባሪዎቹ እንዳይታወቅባቸው እውነተኛዎቹን ማህተሞች በሐሰተኞቹ ቀይረዋል።
መርከቦቹ በባሕር ላይ በነበሩት ወቅት ለአምስት ጭነቶች ሜርኩሪያ ከ36 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከፍሏል።
መርከቦቹ በዚያው ወር መጨረሻ በቻይናው ሊያንጉንግ ወደብ እስኪደርሱ ድረስ መጭበርበሩ አልታወቀም።
"ገዢው በሻጩና በሁለት ተባባሪዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲካሄድ አቤቱታ አቅርቧል ድርጊቱ በተደራጀ መንገድ የተከናወነ የማጭበርበር ውጤት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል" ብሏል የቱርክ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ።
አንድ ነጋዴ የገዛቸው ንብረቶች ካልደረሱት በጭነት ኢንሹራንሱ ፖሊሲ መሠረት ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል። የቱርኩ ኩባንያ ከሰባት ስምምነቶች በአንዱ ብቻ ጭነቱን ለመካስ የሚውል እውነተኛ ኢንሹራንስ እንደሚገባ ሜርኩሪያ ደርሶበታል። የተቀረው በሙሉ የተጭበረበረ ነበር።
ሮይተርስ ለሜርኩሪያ መዳቡን የሸጠውን የቱርክ ኩባንያ ቢኤትሳን ባኪርን ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ችሎቶች በዚህ ሳምንት ይሰማሉ።