በስዊትዘርላንድ የሙስሊም ሴቶች የፊት መሸፈኛ እንዳይደረግ በሕዝበ ውሳኔ ድጋፍ አገኘ

ታትሟል

ስዊትዘርላንድ ውስጥ በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ ሙስሊም ሴቶች የሚያደርጉትን ቡርካና ኒካብን ጨምሮ በአደባባይ ፊት መሸፈኛ ማድረግን የሚከለክለው ሐሳብ በጠባብ የድምጽ ልዩነት አሸነፈ።

በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት 51.2 በመቶ የሚሆኑ ድምጽ ሰጪዎች የፊት መሸፈኛውን ማድረግ የሚከለክለውን ሐሳብ ሲደግፉ 48.8 በመቶ ደግሞ ተቃውመውታል።

ሐሳቡን ያመጣው የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ አቀንቃኙ ስዊዝ ፒፕልስ ፓርቲ ሲሆን "አክራሪነት ይብቃ" የሚሉ መፈክሮች ሲያሰማ ከርሟል።

የስዊዝ እስላማዊ ቡድን ኃላፊ ይህ ለሙስሊሞች "ጨለማ ቀን" ነው ሲሉ ውሳኔውን ገልፀውታል።

"የዛሬው ውሳኔ የከረመ ቁስል መነካካት ነው፤ የእኩልነትን ጉዳይ መልሶ የሚያመጣ ነው። አልፎም አናሳ የሙስሊም ማኅበረሰቦችን በግልፅ የገፋ ነው" ሲል የማዕከላዊ ሙስሊም ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ተቃውሞውን ገልጿል።

የስዊዝ መንግሥት ሴቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው መወሰን የመንግሥት ሥራ አይደለም ሲል ክልከላውን ተቃውሞታል።

ከስዊትዘርላን 8.6 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 5 በመቶ ብቻ ናቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች።

አብዛኞቹ ከቱርክ፣ ከቦስኒያና ከኮሶቮ የመጡ ናቸው።

የጀርመኑ ሉሰርን ዩኒቨርሲቲ ያጠናው ጥናት እንደሚያመልክተው ስዊትዘርላንድ ውስጥ ማንም ሰው ቡርካ አያደርግም፤ ኒካብ የሚያደርጉ ሴቶች ደግሞ በቁጥር 30 ቢሆኑ ነው።

በስዊዝ ቀጥተኛ ዲሞክራሲ ሥርዓት መሠረት ዜጎች በመሰል ጉዳዮች ላይ ሕዝበ ውሳኔ የማድረግ መብት አላቸው።

እስልምናን በተመለከተ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከአስር ዓመት በፊት የስዊዝ ፒፕልስ ፓርቲ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ዜጎች ሚናራ ወይም የመስጂድ ማማዎች እንዳይገነቡ ድምፃቸውን ሰጥተው ነበር።

ይህን ውሳኔ መንግሥት የተቃወመው ሲሆን ተቃዋሚው ፓርቲ ግን ሚናራ የእስልምና መስፋፋት ምልክት ናቸው ሲል ተከራክሮ ነበር።

እሑድ ዕለት የተካሄደው ሕዝብ ውሳኔ የአደባባው ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎች የፊት መሸፈኛ እንዳይደርጉ እንጂ እስልምናን የሚመለከት አይደለም ቢባልም ውሳኔው "የቡርካ ክልከላ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።

ውሳኔው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክን የሚመለከት አይደለም ተብሏል።

ስዊትዘርላንዳዊያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ሕግጋት እስኪነሱ ድረስ ጭምብል [ማስክ] የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

በርካታ ስዊዝ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ክልከላው ሴቶች ምን መልበስ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው የሚያትት ነው በማለት ተቃውመውታል።

ሳኒታ አሜቲ የተባለች ሙስሊም ስዊትዘርላንዳዊ ሕዝበ ውሳኔው ከመደረጉ በፊት የነበረው ቅስቀሳ ሙስሊም ሴቶችን በመጥፎ ሁኔታ ስሏል ስትል ለቢቢሲ ተናገራለች።

"በርካታ የስዊዝ ሙስሊሞች እንደተሰደቡ፤ አሊያም እንደተገፉ ነው የሚቆጥሩት፤ ውሳኔው ይሄ ቤታችሁ አይደለም እንደማለት ነው።"

ነገር ግን ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥም ውሳኔውን የደገፉ አልጠፉም።

ኢማም ሙስጠፋ ሜሜቲ ምንም እንኳ ቅስቀሳው "እስልምና ጠል" ቢሆንም ውሳኔው ግን ሙስሊም ሴቶች ስዊትዘርላንድ ውስጥ ነፃነታቸውን እንዲያውጁ የሚያደርግ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ውሳኔው "የሴቶችን መብት የሚጋፋ ነው" ሲል ሐሳቡን አሰምቷል።

የፊት መሸፈኛ ጉዳይ አውሮፓ ውስጥ አነጋጋሪና አከራካሪ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ፈረንሳይ የፊት መሸፈኛ ማድረግ የከለከለች ሲሆን ኔዘርላንድስ፣ ዴንማርክ፣ ኦስትሪያና ቡልጋሪያ በቅርቡ በአደባባይ የፊት መሸፈኛ ማድረግ የሚከለክል ሕግ ለማውጣት ተሰናድተዋል።