ቻይና በአምራች ዘርፍ የዓለም ኃያል ለመሆን 30 ዓመት ይቀረኛል አለች

ታትሟል

ቻይና በአምራች ዘርፍ "የዓለም ኃያል" አገር ለመሆን ቢያንስ 30 ዓመታት ይቀሯታል ሲሉ አንድ የመንግሥት አማካሪ በገዢው ፓርቲ አባላት ስብሰባ ላይ ተናገሩ።

ከመኪና አስከ ሞባይል ስልኮች በማምረት የዓለምን ከአንድ ሦስተኛ በላይ ምርት የምታቀርበው ቻይና በዘርፉ ባለሙያዎች "የዓለማችን ፋብሪካ" ተብላ ብትጠራም አሁን ባለችበት ደረጃ ላይ የረካች አትመስልም።

የቻይና መሪዎች አገራቸው የረቀቁ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለማግኘት በአሜሪካ ላይ ጥገኛ መሆናቸው ስላሳሰበቸው ሳይሆን አይቀርም በሦስት አስርት ዓመታት ሁሉን ምርት በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ያለሙት።

ቻይና ገና በአምራች ዘርፍ የምትፈልግበት ደረጃ ለመድረስ ገና ነች ያሉት የመንግሥት አማካሪ ማኦ ዊ "በመሠረታዊ ብቃት በኩል ገና ደካማ ነን" ብለዋል።

"ቁልፍ ቴክኖሎጂዎች በሌሎች አገራት እጅ ውስጥ ናቸው" ስለዚህም ቻይና በዚህ ዘርፍ ለአደጋ የተጋለጠች ናት ሲሉ ለአስር ዓመታት ያህል የአገሪቱ የኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩትና አሁን የቻይና መንግሥት አማካሪ የሆኑት ዊ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ቻይና በከፍተኛ ደረጃ የፍጆታና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እያቀረበች ብትሆንም፤ የምርት ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ እየቀነሰ መሆኑ ይነገራል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የምርቱ ዘርፍ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ከአንድ አራተኛው በጥቂቱ ከፍ ያለ ድርሻ እንደነበረው ተመዝግቧል፤ ይህም ከስምንት ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛው ነው።

"በቅርብ ዓመታት ውስጥ የቻይና የምርት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ታላላቅ እመርታዎችን ቢያስመዘግብም፤ አሁን ያለው ግዙፍ ነገር ግን ጠንካራ ያልሆነ፣ ሁሉን አቀፍ ነገር ግን የላቀ አለመሆኑ በመሠረታዊነት ለውጥ እንዳያመጣ አድርጎታል" ብለዋል አማካሪው።

በዚህም ምክንያት ቻይና በረቀቀ ቴክኖሎጂ ምርት ዘርፍ ያላትን ድርሻ ለማጎልበት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል ረቂቅ የምጣኔ ሀብት ዕቅድ አዘጋጅታለች።

ይህም የሆነው በትራምፕ አስተዳደር ዘመን ቻይና የአሜሪካንን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዳታገኝ በተደጋጋሚ የተጣለባትን እገዳ ተከትሎ ነው። በዚህም ሁዋዌን የመሳሰሉ የቻይና ኩባንያዎች ወሳኝ የሆኑ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን ከአሜሪካ ተቋነት እንዳይገዙ ታግደው ነበር።

አሁን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን የሚያመርቱ ተቋማትን ማቋቋም የቻይና መሪዎች ቀዳሚ ትኩረት ሆኗል።

በአምሰት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ሰባት ለብሔራዊ ደኅንነቷ ወሳኝ የሆኑ የምርት ዘርፎች ተለዩ ሲሆን ይህም የሰው ሰራሽ ልኅቀትና የአየር በረራ ዘርፍን ጨምሮ ሌሎችንም ያካተተ ነው።

የቀረበው ዕቅድ እንዳመለከተው ቻይና አሁን ካላት የአምራች ዘርፍ በተጨማሪ በአውሮፕላን ምርት፣ በሮቦት ሳይንስ ዘርፍና አዲስ ኃይል በሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መስክ ያላትን ተወዳዳሪነት ከፍ የማድረግ አላማን ይዟል።