ከአሜሪካ ተባሮ ቻይና መንኩራኩር እንድታመጥቅ የረዳው ተመራማሪ

ታትሟል

ቻይናዊው ሳይንቲስት ሁለቱ የዓለማችን ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤቶች ወደ ጨረቃ እንዲጓዙ ከፍተኛ አስተዋጽኦን አበርክቷል።

ነገር ግን የዚህ ሳይንቲስት ስም በአግባቡ ተመዝግቦ የሚገኘው በአንድ አገር ብቻ ነው።

በቻይናዋ ሻንግሃይ ውስጥ 70 ሺ ቅርሶችን የያዘ አንድ ሙዝየም በሙሉ ለእሱ ማስታወሻ እንዲሆን ተደርጓል። ''የህዝብ ተመራማሪ'' በመባልም ነው የሚጠራው፤ ሺያን ሺንሰን ።

ተመራማሪው ሺያን የቻይና ሚሳኤል እና የሕዋ ምርምር ፕሮግራም አባት ነው ይባላል። የእርሱ የምርምር ስራዎች ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ መንኩራኩሮችን ወደ ህዋ ስታመጥቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በተጨማሪም የቻይና የኒዩክሌር ፕሮግራም አካል የሆነው ሚሳኤልም የእርሱ የምርምር እጅ አለበት። ለዚህም ነው ይህ ሰው በቻይናውያን ዘንድ እንደ ብሄራዊ ጀግና የሚቆጠረው።

ነገር ግን የመጀመሪያ ትምህርቱን የተከታተለባትና ከአስር ዓመታት በላይ በስራ ያሳለፈባት ሌላኛዋ ታላቅ አገር ግን ስራዎቹን እምብዛም አታስታውሳቸውም። ከነጭራሹም የተረሳ ይመስላል።

ሺያን ሺንሰን የተወለደው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1911 ላይ ሲሆን በወቅቱ ቻይና ከንጉሳዊ አገዛዝ ወደ ሪፐብሊክ ልትሸጋገር የመጨረሻዎቹ ዓመታት ላይ ነበረች። ሁለቱም ወላጆቹ ቀለም ቀመስ ሲሆኑ ጃፓን ውስጥ ይሰሩ ነበር። የቻይናን የትምህርት ስርአትምን መስመር ያሲያዙት የሺያን ወላጆች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ገና ከልጅነቱ ኪያን ብሩህ አእምሮን የታደለ ልጅ ነበር። በሻንግሃይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርሲቲም ከክፍሉ ከፍተኛውን ነጥብ በማምጣት አሜሪካ በሚገኘው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የትምህርት ዕድል ማግኘት ችሏል።

በዚሁ ማዕከል ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በወቅቱ ትልቅ ቦታ ከነበራቸው ቴዎዶር ቮን ካርማን ስር ለማጥናት ወደ ካሊፎርኒያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ተዘዋወረ።

በዚሁም 'ሱውሳይድ ስኳድ' የሚል ቅጽል ስም የተሰጠውን የተመራማሪዎች ቡድን ለመቀላቀል ቻለ።

ይህ የተመራማሪዎች ቡድን ቀስ በቀስ እውቅናን እየታረፈና በርካታ የምርመር ስራዎችን መስራቱን ቀጠለበት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑ የሮኬት ማስወንጨፊያ ሞተሮች ላይ ምርም በማድረግና ሙከራ መስራት ጀመረ።

በወቅቱ ሮኬት ሳይንስ ብዙ ተመራማሪዎች የማይደፍሩትና በቁምነገር የማይከታተሉት ዘርፍ ነበር። ነገር ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመር በኋላ የሮኬት ሳይንስ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጣ።

በዚህም ምክንያት ሺያን ሺንሰን አባል የሆነበት የተመራማሪዎች ቡድን የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋምን ትኩረት መሳብ ቻለ። በርካታ ምርምሮቻቸውም በተቋሙ በኩል የገንዘብ ድጋፍና ትብብር ይደረግላቸው ጀመር።

1943 ላይም ሺያን እና ጓደኞቹ የጀት ማስወንጨፊያ ቤተ ሙከራን ማቋቋም ቻሉ።

ምንም እንኳን ኪያን ዜግነቱ ቻይናዊ በሆንም በወቅቱ አሜሪካና ቻይና ወዳጆች ስለነበሩ ማንም ግድ የሰጠው አልነበረም። እንደውም በርካታ የሕዋ ምርምሮችን እንዲያካሂድና እንዲመራ ከፍተኛ የደህንነት ፍቃድ ተሰጠው።

የአሜሪካ ሳይንስ አማካሪ ቦርድ ውስጥም አባል ሆኖ አገልግሏል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ ኪያን በዘርፉ አሉ ከሚባሉ ተመራማሪዎች መካከል አንዱ መሆን ቻለ። ከእውቁ ማሃንዲስ ቴዎዶር ቮን ካርማን ጋር በመሆን ለአንድ ግዳጅ ወደ ጀርመን ተልከውም ነበር።

ዋና ዓላማቸው የጀርመን ኤንጂነሮችን ማነጋገርና ጀርምን በዘርፉ ምን ያክል እውቀት እንዳላት ማወቅ ነበር። በዚህ ስራቸውም ሁለቱ ተመራማሪዎች ትልቅ እውቅናና ክብር ማግኘት ችለዋል።

ነገር ግን ኪያን አስር ዓመታትን በአሜሪካ በዚህ መልኩ ካሳለፈ በኋላ ከሙያው ጋር ያልተያያዙ ጋሬጣዎች መከሰት ጀመሩ።

1949 ላይ ዋና ጸሀፊው ማኦ የቻይና ህዝቦች ኮሚዩኒስት ሪፐብሊክ መመስረትን አወጁ። ወዲያውም ቻይና አሜሪካን በእርኩስ ጠላትነት አወጀች።

አሜሪካ ቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የአሜሪካው ፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ሺያን ሺንሰን እና ፍራንክ ማሊናን ኮሚዩኒስት እንደሆኑ እና ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት እንደሆኑ አወጀ።

በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዡዮ ዋንግ እንደሚሉት ሺያን የኮሚዩኒስት ፓርቲ አባል ስለመሆኑና ለቻይና ስለመሰለሉ ምንም አይነት መረጃ በወቅቱ ማቅረብ አልተቻለም ነበር።

ነገር ግን ተሰጥቶት የነበረው ከፍተኛ የደህንነት ፈቃድ ከተነጠቀ በኋላ ከአምስት ዓመታት የቤት ውስጥ እስር አሳልፎ በፕሬዝደንት ኤይሰንሆወር ትዕዛዝ ወደ ቻይና እንዲመለስ ተደረገ።

በጀልባ ተጭኖ ከባለቤቱና ሁለት አሜሪካ ከተወለዱ ልጆቹ ጋር ሆኖ ለጋዜጠኞች ሲናገር ከዚህ በኋላ በድጋሚ የአሜሪካን አፈር እንደማይረግጥ ገልጾ ነበር። እንዳለውም አድርጎታል። አሜሪካ ድርሽ አላለም።

ሺያን ሺንሰን ቻይና ሲደርስ የጀግና አቀባበል ነበር የጠበቀው። ነገር ግን ወዲያውኑ የቻይና ኮሚዩንስት ፓርቲን አልተቀላቀለም።

በወቅቱ ቻይና ውስጥ ስለ ሮኬት ሳይንስ የነበረው እውቀት ዝቅተኛ ነበር። ነገር ግን ከ15 ዓመታት ልፋትና ምርምር በኋላ ቻይና የመጀመሪያውን መንኩራኩር ወደ ሕዋ ማምጠቅ ቻለች።

በነበሩት አስርት ዓመታትም በርካታ ተማሪዎችን ያሰለጠነ ሲሆን ቻይና ጨረቃ ላይ ላደረገችው ምርምር የመሰረት ድንጋዩን እንደጣለም ጭምር ይነገርለታል፤ ሺያን ሺንሰን።

በሚያስገርም ሁኔታ በሺያን ልፋት ቻይና ውስጥ የተሰሩት ሮኬቶች በጦርነት ወቅት አሜሪካ ላይ ተተኩሰው ነበር። በ1991ዱ የገልፍ ጦርነት ላይ ቻይና ሰራሽ ሮኬቶች አሜሪካ ላይ ተተኩሰው ነበር።

በአሁኑ ሰአት የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት ከምን ጊዜውም በበለጠ የተካረረበት ወቅት ነው። ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ አሜሪካውያን ስለ ሺያን ሺንሰን ያላቸው እውቀት ውሰን ቢሆንም አሜሪካውያን ትውልደ ቻይናውያን ግን አሁንም እንደ ጀግና ነው የሚቆጥሩት።