ማሪያ ኬሪ በወንድሟ ክስ ተመሰረተባት

ማሪያ ኬሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የማሪያ ኬሪ ታላቅ ወንድም እህቴ በአዲሱ መጽሐፏ ላይ ስሜን አጥፍታለች፣ የአእምሮ ጤናዬን ረብሻዋለች ሲል ክስ መሰረተ።

ሞርጋን ኬሪ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት ባይገልጽም መጽሐፉ ግን በሀሰት አመፀኛ እንደሆንኩ አድርጎ አቅርቦኛል ብሏል።

"የአእምሮ ጤናዬ ተቃውሷል" እና " መልካም ስሜም ጎድፏል" ማለቱ በመሰረተው ክስ ላይ ተመልክቷል።

ይህ ክስ የተመሰረተው የማሪያ ኬሪ እህት የ1.25 ሚሊዮን ዶላር የጉዳት ካሳ ክስ ከመሰረተችባት ከወር በሏላ ነው።

የማሪያ እህት አሊሰን ኬሪ ክሱን የመሰረተችው በዚሁ መጽሐፍ ላይ በመጥፎ ተግባር ስሟ መጠቀሱን ተከትሎ ነው።

አሊሰን በመጽሐፉ ላይ ማሪያ ኬሪ የ12 ዓመት ልጅ እያለች የድብርት መድሃኒት እንደሰጠቻት፣ ከወንዶች ጋር ልታገናኛት እንደሞከረች፣ የፈላ ሻይ እንደደፋችባት በመጥቀስ የጻፈችውን "አሳፋሪ" እና እኔን ለማሸማቀቅ የተደረገ ስትል ገልፀዋለች።

አክላም እህቷ ላቀረበቻቸው ወንጀሎች ሁሉ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላቀረበችም ስትል ገልጻለች።

የማሪያ ሕይወት ታሪክን የሚተርከው ይህ መጽሐፍ ለሕትመት የበቃው ባለፈው መስከረም ወር ሲሆን በጥቅምት ወር በኒውዮርክ የመጽሐፍት ሽያጭ ዝርዝር ላይ ከፍተኛ ገቢ በማስመዝገብ ከላይ ተቀምጧል።

መጽሐፉ ስለማሪያ ህይወት በርካታ ነገሮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን አስተዳደጓ ፈታኝ እንደነበረ፣ በልጅነቷ የገጠማትን ዘረኝነት፣ እናም ከመጀመሪያ የትዳር አጋሯ፣ ቶሚ ሞቶላ ጋር ስለነበራት አለመግባበት በዝርዝር አስፍራለች።

ሞርጋን ኬሪ እርሷ ታዳጊ እያለች ከአባቱ ጋር የነበረውን ተደጋጋሚ አለመግባባት በመጥቀስ ስሜን አጉድፋዋለች ብሏል።

ማሪያ በመጽሐፏ ላይ "አባቴን እና ወንድሜን ለመገላገል 12 ፖሊሶች ተሳትፈው ነበር" ያለች ሲሆን ሞርጋን ግን ይህ ልብ ወለድ ነው በቤት ውስጥ ለተነሳ አነስተኛ ጠብ ከአንድ ወይም ሁለት ፖሊስ በላይ አያስፈልግም ብሏል።

ማሪያ በመጽሐፏ ላይ ታዋቂ ከሆነች በኋላ ወንድሟ ከእርሷ ገንዘብ ለመውሰድ ይሞክር ነበር በማለት ይህም "በወንጀል መመዝገቡን" አስፍራለች።

ሞርጋን በመሰረተው ክስ ላይ በማሪያ የሀሰት ውንጀላ እና ክስ መናደዱን አስፍሯል።

"ምንም ቢሆን እህቱ በጥበቡ አለም እና በግሏ ስኬት ሊቀና አይችልም። በግሉም ሆነ በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ነው፤ ለእርሷም መልካሙን ሁሉ የሚመኝ ነበር" ሲል የክስ መዝገቡ አስነብቧል።

ከማሪያ ጋር በክሱ ላይ ስማቸው የተጠቀሰው መጽሐፉን በጋራ የጻፈችው ሚሼላ አንጀላ ዴቪስ፣ አሳታሚው ማክሚላን እና አንዲ ኮህን ቡክስ ናቸው።

ነገር ግን ማንኛቸውም ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።