ኮሮናቫይረስ፡ በቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ሐሰተኛ ክትባቶችን ፖሊስ ያዘ

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካ እና የቻይና ፖሊሶች በሺዎች የሚቆጠሩና ተመሳስለው የተሰሩ ሕገወጥ የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን መያዛቸውንና በአስርታት የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዓለማቀፉ የፖሊስ ጥምረት ኢንተርፖል አስታወቀ።

ቻይና ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ትክክለኛ ያልሆኑ ክትባቶችን ሲያዘጋጁ ነበር የተባሉ 80 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከ3 ሺህ በላይ ክትባቶች ደግሞ በቦታው ላይ ተገኝተዋል ተብሏል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ሶስት የቻይና ዜግነት ያላቸው ግለሰቦችና አንድ ዛምቢያዊ ጋውታንግ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች ጋር ደግሞ 2 ሺ 400 የክትባት ብልቃጦች ተገኝተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉባቸው ትክክለኛ ቦታዎች እስካሁን ግልጽ አልተደረጉም። በደቡብ አፍሪካ በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ሰዎች የዘገበው 'ሰንደይ ታይምስ' የተባለው ጋዜጣ ነው።

ኢንተርፖል ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ ሀሰተኛ ክትባቶችን ስለሚያዘዋውሩ የወንጀል ቡድኖች ጥቆማ እንደደረሰው አስታውቋል።

እስካሁን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከ2.5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን 115 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል ይላል የጆንስ ሆፕኪንስ ዪኒቨርሲቲ መረጃ።

ኢንተርፖል እንዳለው በህገወጥ መመንገድ ሲዘዋወሩ ስለነበሩት ክትባቶች ሲሸጡ የነበረው በበይነ መረብ አማካይነት ነው። ነገር ግን በአሁኑ ሰአት የትኛውም አይነት ትክክለኛ የኮሮናቫይረስ ክትባት በበይነመረብ እየተሸጠ አይደለም።

''በበይነ መረብ አማካይነት የሚተዋወቁ ማንኛውም አይነት ክትባቶች ትክከለኛ አይደሉም። በተገቢ መልኩ ሙከራ ያልተደረገባቸውና ለጤና ከፍተኛ ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ይሆናሉ'' ብሏል።

በደቡብ አፍሪካዋ ጋውታንግ ግዛት በፖሊስ ከተያዙት 2 ሺ 400 የክትባት ብልቃጦችና አራት ሰዎች በተጨማሪ ትክክለኛ ያልሆኑ 3 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችም ተገኝተዋል።

የአገሪቱ ፖሊስ ብሄራዊ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ቪሽ ናይዶ በወንጀሉ ላይ በመሳተፍ የተጠረጠሩ የውጭ አገራት ዜጎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተሰራው ስራ የኢንተርፖል አባል የሆኑ አገራት ሚና ትልቅ እንደነበር በመግለጽ ስራው ውጤታም ነበር ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ ህዝቧን መከተብ የጀመረችው ባሳለፍነው ወር ሲሆን በአፍሪካ በኮሮረናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።

የቻይና የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ''ከክትባት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ማጭበርበሮችን ለመከላከልና ወንጀለኞችን ለመያዝ ፖሊስ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ ነበር። ከኢንተርፖል ጋር በመሆንም መሰል ተግባራትን ለማስቆም ውጤታማ ስራ እየሰራን ነው'' ብለዋል።

የኢንተርፖል ዋና ጸሀፊ ጀነራል የርገን ስቶክ በቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ከፖሊስ ጋር በጥምረት የተሰራው ስራ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከክትባት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ግን ከዚህም የከፉና ገና ስራው ጅማሬ ላይ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ ድርጅቱ 194 አባል አገራት ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ዝግጅት እንዲያደርጉና ሕገወጥ ክትባቶችን እንዲከታተሉ ማሳሰቢያ አውጥቶ ነበር።

ባሳለፍነው ወር ቻይና ውስጥ የታሸገ ውሀ በብልቃጥ በማድረግ የኮሮረናቫይረስ ክትባት ነው በማለት በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማትረፍ ሲኦንቀሳቀስ የነበረ ቡድን መሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወስ ነው።

ሜክሲኮ ውስጥ ደግሞ በሰሜናዊ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ኑዌቮ ሊዮች ግዛት ፖሊስ ህገወጥ የኮሮረናቫይረስ ክትባቶችን ሲያዘዋውሩ የነበሩ ስድስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

ተጠርጣሪዎቹ እንዳሉት ሐሰተኛ ክትባቶቹን በብልቃጥ እስከ 2 ሺ ዶላር ድረስ ለመሸጥ ነበር ያሰቡት።