ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዌስት ባንክ እና በጋዛ 'የጦር ወንጀል' ምርመራ ተከፈተ
የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ በፍልስጥኤም ግዛቶች ተፈጽሟል በተባሉ የጦር ወንጀሎች ላይ ይፋዊ ምርመራ ከፍቷል፡፡
ምርመራው በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ፣ በምስራቅ ኢየሩሳሌምና በጋዛ ሰርጥ ከጎርጎሮሳዊያኑ ሰኔ 2014 ጀምሮ ያሉትን ክስተቶች እንደሚሸፍን ፋቱ ቤንሱዳ ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ወር በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤት በአካባቢዎቹ የተሰጠውን ስልጣን ሊጠቀምበት እንደሚችል ውሳኔ አስተላልፏል ፡፡
እስራኤል የቤንሱዳን ውሳኔ ውድቅ ስታደርግ የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ግን አወድሰውታል፡፡
አሜሪካ በተወሰደው እርምጃ መከፋቷን እና ተቃውሞዋን ገልፃለች፡፡
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሮማ ስምምነት መሠረት በተዋቀሩት መንግስታት ግዛት ውስጥ በዘር ማጥፋት፣ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል እና በጦር ወንጀሎች የመክሰስ ስልጣን አለው፡፡
እስራኤል የሮምን ስምምነት ባታጸድቅም የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ የፍልስጥኤማውያንን ስምምነት በ 2015 የተቀበለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ስልጣን እንዳለው ወስኗል፡፡
እስራኤል በ 1967 በተካሄደው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ዌስት ባንክን፣ ጋዛን እና ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ተቆጣጥራለች፡፡ ፍልስጥማውያን ግዛቶቹን ወደፊቱ ገለልተኛ መንግሥት ለመመስረት ይረዱናል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ዐቃቤ ሕግን ያነሳሳው ምንድን ነው?
ቤንሱዳ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ጽሕፈት ቤታቸው "ምርመራ ለመጀመር ምክንያታዊ መሠረት እንዳለ ወስኗል" ብለዋል፡፡
ለአምስት ዓመታት ያህል የዘለቀ "ከባድ ቅድመ ምርመራ" እንዳደረጉ ገልጸው ምርመራው ያለ ፍርሃት በገለልተኛ እና በግልፅ እንደሚከናወን ቃል ገብተዋል፡፡
በሮማ ሕግ መሠረት የተሰጡንን ግዴታዎች በሙያዊ አቋማችን ከማሟላት ውጭ ሌላ አጀንዳ የለንም ያሉት ብለዋል።
"ሆኖም አሁን ያለውን ሁኔታ ለመቀጠል ምክንያታዊ መሠረት መኖሩን እና ተቀባይነት ያላቸው ጉዳዮችም አሉ" ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ምን ምላሽ ተሰጠ?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "የፀረ-ሴማዊነት እና ግብዝነት ያለው ነው" ብለዋል፡፡
"እጅግ አረመኔ የሆኑ አሸባሪዎችን የሚዋጉት ጀግኖች እና ሞራል ያላቸው ወታደሮቻችን የጦር ወንጀለኞች መሆናቸውን አረጋግጧል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"ናዚዎች በአይሁዶች ላይ የፈጸሙት ዘግናኝ ድርጊት እንዳይደገም ለመሥራት የተቋቋመው ፍርድ ቤት አሁን በአይሁድ ህዝብ ላይ እየዞረ ነው" ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፐራይስ ውሳኔውን ተችተዋል፡፡
"ዓቃቤ ህግ በፍልስጤም ሁኔታ ላይ ምርመራ በመክፈቱ ቅር ከመሰኘት በተጨማሪ በጥብቅ እንቃወማለን። እስራኤልን ያለአግባብ ኢላማ ለማድረግ የሚጥሩ ድርጊቶችን በመቃወም ለእስራኤል እና ለደህንነቷ ያለንን ጠንካራ ቁርጠኝነት አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል፡፡
የፍልስጥኤም አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ አል-ማሊኪ በበኩላቸው "የእስራኤል ወረራ መሪዎች በፍልስጤም ህዝብ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ እና የተፈጸሙ ስልታዊ እና የተስፋፉ ወንጀሎችን መመርመር አስፈላጊ እና አስቸኳይ ነው" ብለዋል፡፡
ጋዛን የሚቆጣጠረው ታጣቂው የሃማስ እንቅስቃሴ ውሳኔውን "በፍትህ ማምጣት ጎዳና ላይ ወደፊት መራመድ" ሲል የተቀበለ ሲሆን ድርጊቱን እንደ "ህጋዊ ተቃውሞ" ይከላከልልናል ፡፡
የሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ "ሁሉም ዓይኖች ወደ ዓቃቤ ህጉ ይዞራሉ። የአይ ሲ ሲ አባል አገራት የፍርድ ቤቱን ሥራ ከማንኛውም የፖለቲካ ጫና ለመጠበቅ ዝግጁ መሆን አለባቸው" ብለዋል፡፡
የትኞቹ የወንጀል ድርጊቶች ይመረመራሉ?
የቤንሱዳ የመጀመሪያ ምርመራ እንደ ጋዛ ባሉ አካባቢዎች የእስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እና በዌስት ባንክ የአይሁድ ሰፈራዎች ግንባታን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ይታመናል።
የቅድመ ምርመራውን ተከትሎም ቤንሱዳ የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያታዊ መሠረት እንዳለ ገልፀው በእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት ባልደረቦች፣ በሃማስ አባላት እና በሌሎች የፍልስጤም ታጣቂዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ይችላል ብለዋል፡፡ .
በተጨማሪም እስራኤል ዌስት ባንክን በወረረችበት ወቅት የእስራኤል ባለሥልጣናት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ብሎ ለማመን ምክንያታዊ መሠረት አለ ሲል ደምድሟል ፡፡