በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት በአስር ሺዎች ደብዛቸው መጥፋቱን ተመድ አሳወቀ

የጠፉ ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች መጥፋታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባደረግኩት ምርመራ ደርሸበታለሁ ብሏል።

እነዚህ ዜጎች ባለፉት አስር አመታት ደብዛቸው መጥፋቱንም አጋልጧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በሶሪያው ጦርነት ተፈፀሙ ያላቸውን የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ዘርዝሯል።

ሪፖርቱ እንደሚያትተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት እንደተገደሉ እንዲሁም አሰቃቂ ወንጀሎች ተፈፅሞባቸዋል ብሏል። ለዚህም ደግሞ ሁለቱንም አካላት ጥፋተኛ አድርጓል።

የጥቃቱ ሰለባና የአይን እማኞች ለመስማት የሚዘገንኑ ወንጀሎች እንደተፈፀሙ ለድርጅቱ አስታውቀው ዕድሜያቸው አስራ አንድ የሚገመቱ ህፃናት ሴቶችና ወንዶች ተደፍረዋል ብለዋል።

በሪፖርቱም ላይ አጠቃላይ እንደ አገር የደረሰውን ስቃይ የገመገመ ሲሆን ሁኔታውም በብሔራዊ ደረጃ ሊታይ እንደሚገባው አስምሯል።

በአውሮፓውያኑ 2011 በመንግሥት ላይ የተነሳውን ሰላማዊ ተቃውሞ ዝም ለማሰኘት ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ ያልተገባ ኃይል መጠቀማቸውን ተከትሎ አገሪቷ በጦርነት ስትናወጥ ቆይታለች።

ጦርነቱ 380 ሺህ ዜጎቿን ሲቀጥፍ የአገሪቷን ግማሽ ህዝብም ከቀዬው እንዲሰደድ አድርጎታል። ከነዚህም ውስጥ 6 ሚሊዮን ስደተኞች በውጭ አገራት ይኖራሉ።

የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ አለም አቀፍ ነፃ አጣሪ ኮሚሽን በሶሪያ ላይ ይህንን ሪፖርት ለማዘጋጀት 2 ሺህ 650 ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል። እንዲሁም 100 የሚሆኑ የማቆያ ስፍራዎች ላይ ምርመራ አድርጓል።

በጦርነቱ ላይ ተሳትፈዋል የሚባሉ አካላት በሙሉ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማንበርከክ በሚል ከፍተኛ ጥሰቶችን እንዳደረሱም መዝግቧል።

"የመንግሥት ኃይሎች በዘፈቀደ ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ሰልፈኞችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የግጭቱም ዋነኛ መንስኤ ነበር" በማለት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ፖውሊ ፒንሄይሮ ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጃቸው ቡድኖች መካከል ሃያት ታህሪር አል ሻምና እስላሚክ ስቴት ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ "አሰቃቂ የሚባሉ ጥሰቶችን ፈፅመዋል" በማለት ሪፖርቱ አትቷል።

በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦች ለወራት ያህል በጨለማ ክፍል ተዘግቶባቸው እንደነበር፣ ቆሻሻ ውሃ እንዲጠጡ፣ የበሰበሰ ምግብ እንዲመገቡ መደረጋቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሽንት ቤት በሌለባትና በተጨናነቀች ክፍል ተዘግቶብን ነበር ሲሉ ለተመድ ተናግረዋል።

በርካቶችም ህክምና እንዳያገኙም መከልከላቸውን እንዲሁ አስታውቀዋል።

በተለይም በመንግሥት ስር ባሉ እስር ቤቶች ግለሰቦች መረጃ እንዲያወጡ በሚል የፀጥታ ኃይሎች ኢ-ሰብዓዊ የሚባሉ የማሰቃያ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል ብለዋል።

ከነዚህም መካከል የኤሌክትሪክ ሾክ፣ ጥፍር ነቀላ፣ የተወሰነውን የሰውነት የአካል ክፍል በእሳት ማቃጠል እንዲሁም ለረዥም ሰዓት ገልብጦ መስቀል የመሳሰሉት መድረሳቸውን አሳውቀዋል።

"በከፍተኛ ሁኔታ አሰቃዩኝ፤ ማንም ሳያውቅ እዚሁ መግደል እንችላለን " በማለት ስቃይ የደረሰበት ግለሰብ ለተመድ መናገሩም ሰፍሯል።