ሃይቲ፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች ሃይቲ ከሚገኝ እስር ቤት አመለጡ

ታትሟል

በሰሜን አሜሪካዊቷ አገር ሃይቲ፤ ከ400 በላይ ታራሚዎች ከዋና መዲናዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ አቅራቢያ ከሚገኝ እስር ቤት ማምለጣቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ማክሰኞ እለት እስረኞቹ ከክሮክስ ደስ በኮትስ እስር ቤት በጅምላ ማምለጣቸውን ተከትሎ የእስር ቤቱን ዳሬክተር ጨምሮ የ25 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ከሟቾቹ መካከል በአካባቢ የነበሩ ንፁሃን ሰዎች እንደሚገኙበት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ከእስር ቤቱ ካመለጡት መካከል ነውጠኛ የሚባል የወሮበሎች ቡድን ይመራ የነበረ አርኔል ጆሴፍ የተባለ ግለሰብ የነበረበት ሲሆን ካመለጠ ከሰዓታት በኋላ ተገድሏል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ገሪይ ደስሮሴርስ፤ ጆሴፍ የእስረኞች የእግር ካቴና ሳያወልቅ መንገደኛ መስሎ በሞተር ሳይክል ሲጓዝ ነበር ብለዋል።

በወቅቱም ሞተር ሳይክሉ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ለመቆም ፈቃደኛ አልነበረም።

በዚህ ጊዜ ጆሴፍ ባለሥልጣናቱ ላይ መሳሪያ አውጥቶ ሲደግን፤ተኩሰው ክፉኛ እንዳቆሰሉት ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

ጆሴፍ እአአ በ2019 ከመያዙ በፊት በሃይቲ ውስጥ በጥብቅ የሚፈለግ የወንበዴዎች መሪ ነበር።

ፖሊስ ወዲያውኑ የተወሰኑ እስረኞችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ቢሆንም፤ በመቶዎች የሚቆጠሩት ግን እስካሁን አልተያዙም።

የእስረኞቹን ማምለት በተመለከተ የወጣ ግልጽ የሆነ ዝርዝር መረጃ የለም።

የዐይን እማኞች ሐሙስ ዕለት እኩለ ቀን ላይ የተኩስ ድምፅ መስማታቸውንና እስረኞች ከእስር ቤቱ እየሮጡ ሲያመልጡ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በአቅራቢያው የሚገኝ የልብስ ልብስ መሸጫ መደብር ሰራተኛም ላመለጡት እስረኞች እቃዎችን ለመስጠት ተገደው እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ክሮክስ ደስ ቦከትስ እስር ቤት የተመረቀው እአአ በ2012 ሲሆን የተሰራው 872 እስረኞችን እንዲይዝ ታስቦ መሆኑን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የሃይቲ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ፍራንዝ ኤግዛንተስም አርብ ዕለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ እስረኞቹ ከማምለጣቸው በፊት፤ ከ1 ሺህ 500 በላይ እስረኞች እንደነበሩ ተናግረዋል።

ኃላፊው "ስድስት እስረኞችንና በሥራ ላይ የነበሩትን የእስር ቤቱ ተቆጣጣሪ ፖል ሄክተር ጆሴፍን ጨምሮ 25 ሰዎች ሞተዋል" ብለዋል።

ከሟቾቹ መካከል እስረኞቹ ሲያመልጡ የገደሏቸው ንጹሃን ዜጎች እንደሚገኙበት አክለዋል።

በካረቢያኗ ድሃ አገር ሃይቲ፤ ከዚህ ቀደምም እንዲሁ እስረኞች በጅምላ አምልጠዋል።

እአአ በ2019 በሃይቲ ደቡባዊ ግዛት በሚገኘው አክዊን እስር ቤት የነበሩ 78 እስረኞች በሙሉ አምልጠዋል።

ይህ የሆነው ፖሊስ ትኩረቱን በአቅራቢያ ይካሄድ በነበረው የፀረ መንግሥት ተቃውሞ ላይ ባደረገበት ወቅት ነው።

ከሁለት ዓመታት በፊት ደግሞ በሰሜን ፖርት ኦው ፕሪንስ ከሚገኘው አርካሄ እስር ቤት ከ170 በላይ ታራሚዎች አምልጠዋል።