ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይና የኤሌክትሪክ መኪኖች ከቴስላ በሽያጭ መብለጣቸው ተነገረ
የቻይና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መኪኖች በገበያው ላይ ተፈላጊ የሆኑትን የቴስላ መኪናዎችን ሽያጭ መብለጣቸው ተነገረ።
መኪኖቹ ረከስ ያሉ ሲሆን ዋጋቸውም 4 ሺህ 500 ዶላር ወይም በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ወደ 180 ሺህ ይሆናል።
የሆንግ ሁዋንግ ሚኒ ኢቪ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው እነዚህ መኪኖች ሽያጭ መመንደግ፤ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ላለውና ከፍተኛ የመኪና አምራች ኩባንያው ሳይክ ሞተር ስኬት አስመዝግቦለታል።
መኪኖቹ እየተመረቱ ያሉት ከሳይክ ሞተርስ በተጨማሪ ሌላኛው አጋር ድርጅትና የአሜሪካው ትልቁ የመኪና አምራች ጄኔራል ሞተርስ ጋር በጥምረት ነው።
በባለፈው ወር እነዚህ የኤሌክትሪክ መኪኖች የቴስላን ሽያጭ እጥፍ ያስመዘገቡ ሲሆን በደህንነታቸው ጉዳይ ላይም አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።
ሆንግ ጉዋንግ ሚኒ የሚል ስያሜ የተሰጠው የሳይክ የኤሌክትሪክ መኪና ታዋቂውና በዋጋው ረከስ ያለው ሞዴል ሲሆን በቅርቡም ኩባንያው ኤይር ኮንዲሽነር በመግጠም 5 ሺህ ዶላር የሚሸጡ መኪኖችን አስተዋውቋል።
መኪኖቹም ማንኛውም ነዋሪ ለትራንስፖርት በየቀኑ ሊገለገልባቸውና ምቹ የሆኑ በሚል ነው እየተዋወቁ ያሉት።
የመኪና ባለሙያዎች እነዚህ ምርቶች ከቴስላ ጋር ሲነፃፀሩ በባትሪያቸው፣ በአቅማቸው ደከም ያሉ ቢሆኑም ዋጋቸው ርካሽ በመሆኑና ምቹ በመሆናቸው በሽያጭ ደረጃ የቁንጮነቱን ስፍራ መቆናጠጥ ችለዋል።
በባለፈው አመት ለገበያ የበቁት እነዚህ መኪኖች በአማካኝ 100 ኪሎ ሜትር በሰዓት ፍጥነት ያላቸው ሲሆኑ መያዝ የሚችሉትም ተጠጋግቶ አራት ሰው ብቻ ነው።
"የቻይና መንግሥት የአየር ብክለትን ለመቀነስ ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በአለም ላይ የሳይንስና ፈጠራን በመጠቀም የተሰሩ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በማስተዋወቅ የቀዳሚነቱን ስፍራ መያዝ ይፈልጋል" በማለት የቻይና የገበያዎች የምርምር ቡድን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሻውን ሬይን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሆንግ ሁዋንግ ሚኒ ኢቪን ለማስተዋወቅ የቻይና መንግሥት የመኪና ሰሌዳ ቁጥር በነፃ እየሰጠ ሲሆን ዋስትና አለውም ብሏል። በተለያዩ ከተሞች በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን የሰሌዳ ቁጥር ለማግኘት ወራት እንዲሁም አመታት ይፈጃል ተብሏል።