ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብፅ በደረሰ የጀልባ አደጋ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ጠፉ
በግብፅ አንዲት ጀልባ ሰጥማ የሰዎች ሕይወት አለፈ።
የቤተሰብ አባላትን አሳፍራ የነበረችው ጀልባ ሰጥማ በደረሰ አደጋ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ 7 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።
አደጋው ሰኞ ሌሊት በአሌክሳንደሪያ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ማሪኦት ሐይቅ ላይ ነው የደረሰው።
ጀልባዋ 20 የሚሆኑ ሰዎችን አሳፍራ ነበር ተብሏል። በጀልባዋ ላይ ተሳፈረው የነበሩት ሁሉም የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ተገልጿል።
የነፍስ አድን ሰራተኞች እስካሁን ሰባት ሰዎችን በሕይወት ማግኘት ችለዋል። ከእነዚህ መካከል አምስቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ለሕክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
በርካታ አምቡላንሶችና የነፍስ አድን ሰራተኞችም በስፍራው ተሰማርተው፤ የጠፉትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
እስካሁን የአደጋው መንስዔ አልታወቀም።
ይሁን እንጂ የአሌክሳንደሪያ አስተዳዳሪ መሃመድ ኢል ሻሪፍ፤ ጀልባዋ አስፈላጊውን ፈቃድ ሳታገኝ ለመዝናኛ አገልግሎት ስትውል እንደነበር ገልፀዋል።
አስተዳዳሪው ስለ አደጋው መንስኤ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም።
የአካባቢው ምንጮች በበኩላቸው ጀልባዋ ከአቅም በላይ ጭና እንደነበርና የአየር ፀባዩም ያልተረጋጋ እንደነበር ተናግረዋል።
የማሪኦት ሐይቅ አሌክሳንድሪያ ለሚኖሩ ሰዎች ለሽርሽርና የውሃ ላይ ጉዞ ለማድረግ የሚመርጡት ታዋቂ መዳረሻ ቦታ ነው።