የኮንጎው ፕሬዘዳንት የአምባሳደሩን ግድያ የሚመረምር ልዩ ቡድን አቋቋሙ

አምባሳደር ሉቻ አታናሲዮ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የኮንጎው ፕሬዘዳንት ትላንት በምስራቃዊ ኮንጎ ጎማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ያለፈውን የጣሊያኑን አምባሳደር ሉቻ አታናሲዮ ግድያ የሚመረምር ልዩ ቡድን አዋቀሩ።

በፕሬዘደንቱ የተቋቋመው ቡድን ዛሬ ወደ ጎማ የሚያመራ ሲሆን በቀጥታ ለፕሬዘዳንት ፊሊክስ ሺሺኬዲ ሪፖርት የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል።

"የፕሬዘዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ማክሰኞ የካቲት 16፣ 2013 ዓ.ም ወደ ጣሊያን በመጓዝ የፕሬዘዳንቱን ደብዳቤ ለጣሊያን ምክር ቤት የሚያቀርቡ ይሆናል" ሲል የፕሬዘዳንቱ የፕሬስ ሪፖርት አስረድቷል።

አምባሳደር ሉቻ አታናሲዮ የተገደሉት ከዓለም ምግብ ድርጅት ቡድን ጋር ወደ ጎማ ለጉብኝት ባመሩበት ወቅት ነበር።

አምባሳደሩ በጥቃቱ "ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉን" የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

ፕሬዘዳንት ፊሊክስ ሺሺኬዲ በትዊተር ገፃቸው የጣሊያናዊው ዲፕሎማት ሉቻ አታናሲዮ ግድያ እንዳሳሰባቸው ገልፀው ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዑክ ጋር አብረው ሲጓዙ የደረሰውን "የሽብር ጥቃት" አውግዘዋል።

ፕሬዘዳንቱ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት በወንጀሉ ምርመራ ላይ እንዲረባረቡ እና አጥቂዎችን በመለየት ለፍርድ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በተያያዘ ዜና አምባሳደሩን ገድሏል የተባለው ታጣቂ ቡድን በአምባሳደሩ ግድያ 'እጄ የለበትም' ብሏል።

ዲሞክራቲክ ፎርድ ፎር ዘ ሊብሬሽን ኦፍ ሩዋንዳ የተሰኘው የሁቱ አማጺ ቡድን አምባሳደሩን ገድሏል ተብሎ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንሰትር ተወንጅሎ ነበር።

ይሁን እንጂ የአማጺ ቡድኑ ቃል አቀባይ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

"ከመቶ በላይ ታጣቂ ቡድኖች በስፍራው ይንቀሳቀሳሉ እኛን ለመወንጀል ለምን እንደፈለጉ ሊገባን አልቻለም። በዚህ ግድያ የእኛ እጅ የለበትም" ሲል የአማጺ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኪዩር ንጎማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።