በአሜሪካ አዲስ የሚወለድ ልጅን ጾታ ይፋ ለማድረግ የተገጣጠመ መሳሪያ ፈንድቶ አባትየውን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
በኒውዮርክ የልጅ አባት ለመሆን ጥቂት ጊዜ የቀረው አባት የልጁን ጾታ ይፋ ለማድረግ የገጣጠመው መሳሪያ ፈንድቶ ሕይወቱን መቅጠፉን ፖሊስ አስታወቀ።
እሁድ ዕለት የኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ በቅርቡ የልጅ አባት በመሆኑ የተሰማውን ደስታ ለመግለጽ ወዳጅ ዘመዶቹን ጠርቶ ተፍ ተፍ እያለ እንደነበር ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።
ይህንንም አስመልክቶ ለወዳጅ ዘመድ የጽንሱን ጾታ ለመንገር መለስተኛ ድግስ ሲያዘጋጅ አብረውት ወንድሞቹም ነበሩ።
በዚህ ድግስ ላይ የሚወለደውን ልጅ ጾታ ይፋ ለማድረግ የሚያስችለውን መሳሪያ አባት የገጣጠመው ሲሆን፤ ነገር ግን በድንገት ፈንድቶ ለሞት ሲያበቃው ወንድሙን ደግሞ አቁሱሎታል ይላል የፖሊስ ዘገባ።
ፖሊስ እንዳለው የ28 ዓመቱ ክርስቶፈር ፔክኒ የገጣጠመው መሳሪያ ፈንድቶ የገደለው ሲሆን የ27 ዓመቱን ወንድሙን ማይክል ፔክኒን ደግሞ አቁስሎታል።
ጾታን ይፋ ለማድረግ የሚዘጋጁ ድግሶች በአሜሪካ አደጋ ሲያደርሱ ይህ አዲስ አይደለም ተብሏል።
ፖሊስ እሁድ እለት ፍንዳታውን ያስከተለው ምን ዓይነት መሳሪያ እንደሆነ እስካሁን ድረስ ይፋ አላደረገም።
የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ እና የፈንጂ አምካኝ ቡድኖች ግን በጋራ ምርመራ እያደረጉ መሆኑ ግን ታውቋል።
የከተማዋ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለኒውዮርክ ታይምስ እንደገለፁት የተገጣጠመው መሳሪያ ቱቦ መሰል ነገር ይዞ ነበር በማለት ተናግረው ዝርዝረር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አንድ ወንድሙን በሞት ያጣውና ሌላኛው ወንድሙ ቆስሎ ሆስፒታል የገባው ፒተር ፔክኒ ጁኒየር፣ የተከሰተውን ለጋዜጣው ሲያስረዳ "ከማስበውና ከምገምተው በላይ አስፈሪ አደጋ ነበር" በማለት ፍንዳታውን ምን እንዳስከተለው እንደማያውቅ ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም ጾታን ይፋ ለማድረግ ተብለው በተዘጋጁ ድግሶች ላይ በደረሱ አደጋዎች ሞት ተመዝግቦ ያውቃል።
በአሜሪካ ጾታን ይፋ ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የመገመት ጨዋታ በኋላም ርችት እና በቀለም የተሞላ ጭስ ያለበት ፍንዳታ ይከተላል።
ነገር ግን በርካታ ትልልቅ ድግሶች ላይ አደጋዎች ከዚያም ሞቶችም ይከሰታሉ።
በዚህ ወር በሚቺጋን አዲስ ለሚወለድ ልጃቸው በተዘጋጀ የእንኳን ደስ አለን ድግስ ላይ ከተተኮሰ ርችት የተፈናጠረ ሹል ነገር ለአንድ ሰው ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
በካሊፎርኒያ ደግሞ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር እና በ2017 ሚያዚያ ወር ላይ ለተነሳ ሰደድ እሳት ሁለት የተፀነሰውን ልጅ ጾታ ይፋ ለማድረግ የተደገሱ ድግሶች ሰበብ መሆናቸው ተመዝግቦ ይገኛል።
በወቅቱ በካሊፎርኒያ ኤል ዶራዶ የደረሰው የእሳት አደጋ ከ19 ሺህ ኤከር በላይ መሬት አቃጥሎ በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ በርካታ ቤቶች እንዲቃጠሉ አድርጓል።












