በሕንድ ሁለት ታዳጊ ሴቶች ማሳ ውስጥ ሞተው ተገኙ

በሕንድ ሁለት ታዳጊ ሴቶች ማሳ ውስጥ ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

እድሜያቸው 13 እና 16 የሆኑ ሁለት ታዳጊ ሴት ህጻናት በሕንዷ ሰሜናዊ ግዛት ኡታር ፕራዴሽ ኡኖዋ ክልል ውስጥ በሚገኝ ማሳ ውስጥ አስክሬናቸው መገኘቱ ተገልጿል።

ሌላ የ17 ዓመት ታዳጊ ደግሞ በተመሳሳይ ቦታ ላይ የተገኘች ሲሆን የጤናዋ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ምክንያት በአሁኑ ሰአት በሆስፒታል ለሕይወቷ እየታገለች ነው ተብሏል።

ሦስቱም ታዳጊዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ የ16 እና የ17 ዓመት ታዳጊዎቹ እህትማማቾች ናቸው። የ13 ዓመት ታዳጊዋ ደግሞ የአጎታቸው ልጅ እንደሆነች ተገልጿል።

ቤተሰቦቻቸው እንደሚሉት የታዳጊዎቹን አስክሬን ያገኙት ረቡዕ ምሽት ሲሆን በወቅቱ ሦስቱም እጃቸውና እግራቸው በራሳቸው ልብስ ጥፍንግ ተደርጎ ታስረው ነበር።

ረቡዕ ከሰአት አካባቢ ሦስቱ ታዳጊዎች ለከብቶች መኖ ለማምጣት ነበር ወደ እርሻ ማሳው የሄዱት። መኖ ለማምጣት በሄዱት ሳይመለሱ መቅረታቸውን ተከትሎም ቤተሰቦቻቸው ፍለጋ ወጥተዋል።

የአካባቢው ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ እንዳሉት ታዳጊ ሴቶቹ የሞቱት ተመርዘው ሊሆን ይችላል።

''ከአፋቸው ውስጥ የሆነ ነጭ ነገር ሲወጣ ተመልክተናል። ዶክተሮችም ቢሆኑ የመመረዝ ምልክቶች ማስተዋላቸውን ነግረውናል። ሁሉም የሚመለከታቸውን ሰዎች እያነጋገርን ነው። ማድረግ የሚገባንንና መውሰድ የሚገባንን እርምጃ እየወሰድን ነው'' ብለዋል ሱፐር ኢንተንደንት ሱርሽራዎ አ ኩልካርሚ።

ታዳጊዎቹ 'ዳሊት' ተብለው የሚታወቁት የማህበረሰብ አባላት ሲሆኑ፤ ሕንድ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የማህበረሰብ ክፍፍል ምክንያት ሌሎች ሰዎች ለመንካት እንኳን የሚጸየፏቸው ናቸው።

ምንም እንኳን የሕንድ መንግስት እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ደህንነት ለመጠበቅ የተለያዩ ሕጎችን ቢያስተዋውቅም አሁንም ድረስ ከፍተኛ መገለልና መድልዎ ይደርስባቸዋል።

ኡታር ፕራዴሽ ውስጥ የምትገኘው ኡኖዋ ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሴቶች ላይ በሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ስሟ በተደጋጋሚ እየተነሳ ይገኛል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ አንዲት ሴት ደፋሪዎቿ ላይ ፍርድ ቤት ልትመሰክር ስትሄድ በእሳት መቃጠሏ የሚታወስ ነው። በደረሰባት ከፍተኛ ጉዳትም ሕይወቷ አልፏል።

በክልሉ ሕግ አውጪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ደግሞ በዛው ዓመት በመድፈር ተከሰው ጥፋተኛ ተብለዋል።