የ99 ዓመቱ ልዑል ፊሊፕ ሆስፒታል መግባታቸው ተነገረ

ልዑል ፊሊፕ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ልዑል ፊሊፕ
ታትሟል

የኤደንብራው ልዑል ፊሊፕ ትላንት ምሽት ህመም ከተሰማቸው በኋላ ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ሆስፒታል እንደገቡ የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት አስታወቀ።

የ99 ዓመቱ ልዑል፤ ለንደን ውስጥ ወደ ሚገኘው ኪንግ ኤድዋርድ የተባለ ሆስፒታል ነው የተወሰዱት። ወደ ሆስፒታሉ ከተወሰዱ በኋላ በሐኪማቸው ምክር መሠረት እዚያው ሆስፒታል እንዲተኙ ተወስኗል።

የቢቢሲ የቤተ መንግሥት ምንጮች እንዳሉት፤ ለጥቂት ቀናት ጤናቸው እክል ቢገጥመውም ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ አይደለም።

ጨምሮም ልዑሉ ለጥቂት ቀናት በሆስፒታሉ እንደሚቆዩ ገልጾ፤ "በመልካም ሁኔታ ላይ ናቸው" ብሏል።

የ94 ዓመቷ ባለቤታቸው ንግሥት ኤልዛቤት ግን በዊንድሰር የሚቆዩ ሲሆን፤ ልዑሉና ንግሥቲቷ በቤተ መንግሥት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት በሐኪሞቻቸው እንደተሰጣቸው ተገልጿል።

ጥንዶቹ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጣለውን ገደብ ያሳለፉት በኢንግላንዱ ዊንድሰር ቤተ መንግሥት ከጥቂት ሠራተኞች ጋር ነው።

ነገሥታቱ ያለፈውን የገና በዓል ያከበሩት እንደቀድሞው በዝነኛው የነገሥታት መቆያ ሳንድራግሀም ሳይሆን በርክሽር በተባለው ቦታ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ሆስፒታል የገቡትን ልዑል ፊሊፕ "መልካሙን ሁሉ እመኝሎታለሁ" ማለታቸውም ተዘግቧል።