'ሴቶች ብዙ ያወራሉ' ያሉት የቶክዮ ኦሊምፒክ ኃላፊ ሥራ ሊለቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቶክዮ ኦሊምፒክስ አዘጋጅ ኮሚቴ ኃላፊ የሆኑት ግለሰብ ሴቶችን አስመልክተው የሰጡትን ፆተኛ አስተያየት ተከትሎ በደረሰባቸው ከፍተኛ ወቀሳ ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ሊለቁ ነው።
የኮሚቴው ኃላፊው የ83 ዓመቱ ዮሺሮ ሞሪ ሴቶች በስብሰባዎች ላይ "በጣም ብዙ ያወራሉ፤ ሴት የቦርድ ኃላፊዎች ያሉበት ስብሰባ በጣም ብዙ ጊዜ ይወስዳል" ሲሉ ተናግረዋል ተብሏል። ዮሺሮ ሞሪ ለሰጡት አስተያየት ይቅርታ ጠይቀው በሰጠሁት አስተያየት ግን ስልጣኔን አለቅም ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ ሞሪ ጫናው በርትቶባቸው ሥልጣናቸውን ሊለቁ ከጫፍ ተቃርበዋል።
. "ለምን ስሜን ለ20 ዓመታት ደበቅኩ?"የቀድሞ የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ነገ አርብ በይፋ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ኃላፊነት እንደሚነሱ ይጠበቃል ሲሉ የጃፓን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሞሪ ሴቶችን በማስመልከት ብዙ ያስወቀሳቸውን ፆተኛ አስተያየት የሰጡት ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የጃፓን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነበር።በስበሰባው ላይ "ሴት የቦርድ አባላትን ቁጥር ለመጨመር ካሰብን ለሚያደርጉት ንግግር የሚሰጣቸው ሰዓት የተወሰነ ሊሆን ይገባል። እነሱ እንደሆነ ቶሎ ተናግሮ የመጨረስ ችግር አለባቸው። በጣም ያናድዳል" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል በማለት የጃፓኑ አሳሂ ሺምቡን ጋዜጣ ዘግቧል።የኦሊምፒክ ኮሚቴ በአሁኑ ወቅት 24 አባላት ያሉት ሲሆን አምስቱ ሴቶች ናቸው።ከትናንት በስቲያ የሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ስብስብ የሞሪን አስተያየት ለመቃወም ባለ ነጭ ቀለም ልብስ ለብሰው ታይተዋል። የሴት የሕግ ባለሙያዎቹን ሃሳብ በመደገፈም በርካቶች ነጭ የመልበስ ዘመቻውን ተቀላቅለዋል። በርካቶችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሞሪ ስልጣናቸው እንዲለቁ እየጠየቁ እና ፊርማ እያሰበሰቡ ነው። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ በነጻ አገልግሎት ለመስጠት ከተመዘገቡ ከ400 በላይ ሰዎች የሰውዬውን ንግግር ተከትሎ ፍቃደኝነታቸውን ስርዘዋል ተብሏል። በፈረንጆቹ ከ2000 እስከ 2001 ለአንድ ዓመት ብቻ ጃፓን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስተዳደሩት ዮሪ ዲፕሎማሲ በራቃቸው አስተያየቶቻቸው ይታወቃሉ።








