መፈንቅለ መንግሥትን የሚቃወሙ የሚየንማር ዜጎች አደባባይ ወጡ

በያንጎን የተደረገው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ የሚልቁ የሚየንማር ዜጎች በዋና ከተማዋ ያንጎን ለ2ኛ ቀን አደባባይ ወጡ።

ሰልፈⶉቹ አደባባይ የወጡት ከሳምንት በፊት ወታደሩ መፈንቅለ መንግሥት ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ሰልፈኞቹ ዲሞክራሲ እስኪሰፍን ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን ይላሉ።

በዋና ከተማዋ ያንጎን አድማ በታኝ ፖሊሶች በዋና ዋና ጎዳናዎች ሰፍረዋል። በተለይም በያንጎን ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ በብዛት ይታያሉ።

በአገሪቱ አሁን ምንም አይነት የኢንተርኔት አገልግሎት የለም።

ባለፈው እሑድ መጠነኛ የተቃውሞ ሰልፎች ታይተው ነበር። ሆኖም ወዲያውኑ ከስመዋል።

በሕዝብ ተመራጭ የነበሩት ሳን ሱ ቺ በቁም እስር ላይ ነው የሚገኙት። ፕሬዝዳንት ዊን ሚይንትም በተመሳሳይ እስር ላይ ናቸው።

አምነስቲ የኢንተርኔት መዘጋቱን የኮነነ ሲሆን መረጃዎች የሚወጡባቸው በሮችን መዝጋት ዜጎች ላይ ለሚደርስ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ማመቻቸት ነው ብሏል።

እስከ አሁን መፈንቅለ መንግሥት ያደረሱት የሰራዊት አባላት በምንም ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጡም።

በሚየንማር መፈንቅለ መንግሥቱ የተደረገው ኤንኤልዲ ፓርቲ የኀዳሩን አገራዊ ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉን ተከትሎ አዲስ የአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ሸንጎ ስብሰባውን ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነበር።

በርካታ በርማዊያን መፈንቅለ መንግሥቱን በፌስቡክ በቀጥታ ተከታትለውታል። ሆኖም ከ3 ቀናት በኋላ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ አዘዋል።

በቀድሞ ስሟ በርማ የምትባለው ሚየንማር በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኝ ሲሆን ከሕንድ፣ ከባንግላዴሽ፣ ከቻይና፣ ከታይላንድ እና ከላኦስ ጋር ትጎራበታለች።

ሚየንማር የሕዝብ ብዛቷ 54 ሚሊዮን ይጠጋል።

የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ሳን ሱ ቺ አባት አገሪቱ ከታላቋ ብሪታኒያ ነጻነቷን ለማግኘት ታደርግ በነበረው ትግል የሞቱ እውቅ ጄኔራል ነበሩ።

ከነጻነት በኋላ አገሪቱን ለዘመናት የመሩት ወታደሮች ሲሆኑ በ2010 ቀስ በቀስ ሁኔታዎች መለወጥ ጀምረው ነበር። በ2015 ምርጫ መደረጉን ተከትሎ የሲቪል አስተዳደር መመሥረት ችሎ ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ ግን በአገሪቱ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተደርጎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ባንግላዲሽ ሸሽተዋል።

በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ አስተዳደራቸው ያደረሰውን ግፍ ለማውገዝ ያልቻሉት የኖቤል ተሸላሚዋ ሳን ሱ ቺ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት የደረሰባቸው ሲሆን በበርካታ ስፍራዎች የተሰጧቸው የክብር ሽልማቶችም ተነጥቀዋል።

ሆኖም ሳን ሱ ቺ በአገሪቱ ቡድሃዎች ዘንድ ትልቅ ተወዳጅነት ያላቸው የ76 ዓመት ሴት ናቸው። ከዕድሜያቸው 15 ዓመታትን ያህል ያሳለፉትም በእስርና በቁም እስር ነበር።

ሳን ሱ ቺ ፖለቲካ ፓርቲያቸው ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ በ2015 ድል ቢያደርግም በይፋ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አልሆኑም።

ይህም የውጭ ዜግነት ያሏቸው ልጆች ስላሏቸው ነው። ያም ሆኖ በይፋ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ባይጠሩም ያንን ተግባር ከጀርባ ሆነው ይፈጽሙና ያስፈጽሙ የነበሩ ፖለቲከኛ ናቸው።

በይፋ የሚጠሩበት ሥልጣን ስቴት ካውንስለር ሲሆን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ግን ዊን ሚየንት ናቸው።

አሁን ሁለቱም በእስር ላይ ይገኛሉ። አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን ሳን ሱ ቺ ያልተፈቀዱ የቴሌኮሚኒኬሽን መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ በህገወጥ መንገድ በማስገባት ተከሰዋል። ሰባት የዎኪቶኪ ስልኮች የሳን ሱ ቺ ቤት ሲበረበር ተገኝቶባቸዋል ተብሏል።