ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የህንድ ተቃውሞ፡ የሪሃና የትዊተር ጽሁፍ የህንድ መንግሥትን አስቆጣ
የሪሃና የትዊተር ጽሁፍ የህንድ መንግሥትን አስቆጣ።
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ሪሃና የህንድ ገበሬዎችን ተቃውሞ አስመልክታ በትዊትር ገጿ ላይ መረጃ ማጋራቷን ተከትሎ የህንድ የገበሬዎች ተቃውሞ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ሆኗል።
በጉዳዩ ላይ መልስ የሰጠው የህንድ መንግሥት የውጭ አገር ግለሰቦች እና ታዋቂ ሰዎች ነገሮችን እያቀጣጠሉ ነው የሚል ክስ አሰምቷል።
ሪሃና የገበሬዎቹን ተቃውሞ የሚደግፍ ጽሁፍ ካጋራች ከሰዓታት በኋላ ወጣቷ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ግሬታ ተንበርግ እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የእህት ልጅ ሚና ሃሪስ የገበሬዎቹን ተቃውሞ ደግፈው ጽሑፍ አጋርተዋል።
መልዕክቶቻቸው በስፋት ተጋርተው በሺዎች የሚቆጠሩ ምላሾችንም አስተናግደዋል።
ገበሬዎቹ በመዲናዋ ደልሂ ድንበር አካባቢ የተወሰኑ የእርሻ ሕጎችን ባለመቀበል ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ዛሬ [ረቡዕ] የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በሰጠው መግለጫ መሰረት ከብዙ ክርክር እና ውይይወት በኋላ በግብርናው ዘርፍ ላይ ማሻሻያ አድርጓል።
መግለጫው "ጉዳዮችን በማህበራዊ ሚዲያ እያጋሩ ለማቀጣጠል መሞከር በተለይም በታዋቂ ሰዎች ዘንድ ሲደረግ ትክክልም አይደለም፣ ኃላፊነት የተሞላበትም አይደለም" ብሏል።
የማክሰኞው የሪሃና ጽሑፍ ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ከሚደረግ የኢንተርኔት መዘጋት ጋር የተያያዘ ነበር።
አዲሱን ሕግ ለመቃወም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የህንድ ገበሬዎች በተሰባሰቡባቸው ሦስት ቦታዎች ላይ ህንድ የሞባይል ኢንተርኔትን አቋርጣለች። መንግሥት ይህንን ያደረገው የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ መሆኑን አስታውቋል።
ተቃውሞው ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበው ባለፈው ሳምንት በተፈጠረው የትራክተር አመጽ ሲሆን በዚህም አንድ የተቃውሞው አባል ሲገደል በርካታ ፖሊሶች ቆስለዋል።
የገበሬዎቹ ዩኒየኖች እና ቡድኖች የደረሰውን ጥፋት ቢያወግዙም የጀመሩትን ተቃውሞ ግን እንደማያቆሙ አስታውቀዋል።
101 ሚሊዮን የትዊተር ተከታይ ያላት ሪሃና "ገበሬዎች ከፖሊሶች ጋር ግጭት እየፈጠሩበት ባለው ሁኔታ ህንድ በደልሂ አቅራቢያ ኢንተርኔት አቋርጣለች" የሚለውን የሲኤንኤን ዜና "ስለምንስ በእዚህ ጉዳይ ላይ ማውራት ተሳነን" የሚል ርዕስ በመስጠት አጋርታለች።
በዚህም ምክንያት ይህ ዜና በሕንድ ሰፊ ሽፋን አግኝቷል።
በእርግጥ ሪሃና ይህንን በማጋራቷ እሰየው ካሉት በተጨማሪ የመንግሥት ደጋፊዎች ደግሞ መንግሥት ሕዝቦቹን ለመደገፍ ያደረገውን ጥረት ማጣጣል ተገቢ አይደለም እያሉ ነው።
ካንጋና ራናውት የተባለች የቦሊውድ ተዋናይ "ገበሬ ስለሆኑ ብቻ ስለእነዚህ ሰዎች ማንም ምንም ማለት አይችልም፤ ምክንያቱም ህንድን ለመከፋፈል እያሞከሩ ያሉ አሸባሪዎች ናቸውና" ከሚል ማጣቀሻ ጋር የሪሃናን መልዕክት በመቃወም አጋርታለች።