ካሚል አሕመዲ፡ ብሪታኒያዊው ምሁር ከኢራን አመልጦ በእግሩ እንግሊዝ ገባ

ብሪታኒያዊው ምሁር በእግሩ ከኢራን አመለጠ

የፎቶው ባለመብት, KAMEEL AHMADY

ታትሟል

በቴህራን አገዛዝ ዘጠኝ ዓመት እሥር ተፈርዶበት የነበረው የብሪታኒያና ኢራን ዜግነት ያለው ምሁር አምልጦ ዩናይትድ ኪንግደም ገብቷል።

ካሚል አሕመዲ ከሁለት ወራት በፊት ነበር ከውጭ ሃገር መንግሥት ጋር አብረሃል ተብሎ እሥር የተፈረደበት።

ምሁሩ ክሱ እውነትነት የለውም ሲል ያጣጥላል።

ካሚል በኢራን ፍርድ ቤት የዘጠኝ ወራት እሥርና የግማሽ ሚሊዮን ፓውንድ ቅጣት ተጥሎበት ነበር።

ነገር ግን ይግባኝ ጠይቆ በዋስ ተለቆ ሳለ ነው የኢራንን ተራራዎች በእግሩ በማቋረጥ ከአብዮታዊው ዘብ አምልጦ ዩኬ የገባው።

ካሚል አሕመዲ ከኩርዲሽ ቤተሰቦቹ ምዕራባዊ ኢራን ውስጥ ነው የተወለደው። 18 ዓመት ሲሞላው ቤተሰቦቹ ወደ እንግሊዝ ለትምህርት ላኩት።

ለበርካታ ዓመታት እንግሊዝ የኖረው ካሚል በኬንት ዩኒቨርሲቲና በሎንዶን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ትምህርቱን ተከታትሏል።

ወደ ኢራን ለበጎ አድራጎት ሥራ ከመመለሱ በፊት ነበር ለብሪታኒያ መንግሥት የዜግነት ይሰጠኝ ማመልከቻ አስገብቶ የሃገሪቱ ዜጋ መሆን የቻለው።

ምሁሩ ኢራን ውስጥ በሕፃናት ጋብቻና እንዲሁም በሴቶች ግርዛት ላይ ጥናት ይሠራል።

ኢራን ውስጥ 13 ዓመት የሆናት ሴት ለጋብቻ ብቁ ናት የሚል ሕግ አለ። ካሚል፤ ኢራናዊያን ሴቶች በልጅነታቸው ማግባት የለባቸውም ብሎ ዘመቻ በመክፈቱ ነው በመንግሥት ዓይን ውስጥ የገባው።

ነገር ግን በፈረንጆቹ ነሃሴ 2019 አንድ ሰው የፖስታ ቤት ሠራተኛ ነኝ ሲል ቤቱን ያንኳኳል። ካሚል በሩን ሲከፍት 16 የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባላት አፋፍሰው ወደ ነውጠኛው ኢቭን እሥር ቤት ይወስዱታል።

ምሁሩ የኢራን መንግሥት ጥርስ የነከሰብኝ የጥምር ዜግነት ባለቤት ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን ኢራንና እንግሊዝ ካላቸው መቃቃር የተነሳ ነው ይላል።

"ኢራን ውስጥ የጥምር ዜግነት ባለቤት መሆን አደጋ አለው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ምሁሩ ኢቭን እሥር ቤት ለሦስት ወራት በቆየበት ወቅት መረጃ የሚያውጣጡት መርማሪዎች 'በጭንቅላቴ ሲጫወቱ ነበር' ይላል።

ከሦስት ወራት እሥር በኋላ ተለቆ ልዩ ጥበቃ እየተደረገለት ፍርዱን እንዲከታተል ተወሰነ።

ባለፈው ታኅሣሥ የዋለው ችሎት ካሚል ከጠብ-አጫሪ የውጭ ሃገር መንግሥት ጋር አብሯል ሲል እሥር ጥሎበት ነበር። አቃቤ ሕግ ምሁሩ ይሠራበት የነበር አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከአሜሪካ መንግሥት ገንዘብ ተቀብሏል ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነትን በማበረታታትም ተከሶ ነበር።

የዘጠኝ ዓመት እሥርና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ፓውንድ የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ካሚል በዋስትና ተለቆ ሳለ ኢራንን ጥሎ ለመፈርጠጥ ወሰነ።

"የጠየቅኩት ይግባኝ ውድቅ ሲሆን ጊዜ ነው ዘጠኝ ዓመት እሥር ቤት ከምበሰብስ ሃገር ጥዬ ብጠፋ ይሻላል ያልኩት። እኔ ከአስር ዓመት በኋላ ከእሥር ከተለቀቅኩ - እሱንም ከለቀቁኝ ልጄ የ15 ዓመት ታዳጊ ሆኖ ይጠብቀኛል ማለት ነው።"

ምሁሩ በጣም ለሚቀርባቸው የቤተሰብ አባላት ብቻ አሳውቆ የኢራንን ተራራዎች በእግሩ ማቆራረጥ ያዘ።

"ፂም መላጫዬን፣ ሙቀት ሰጭ አልባሳት፣ ጥቂት መፃሕፍትና ላፕቶፔን ይዤ ፈረጠጥኩ። ጉዞው በጣም ረዥም፣ በጣም ብርዳማ፣ ጨለማ የሞላውና አስፈሪ ነበር።"

ካሚል አሕመዲ አሁን ብሪታኒያ ውስጥ ቢሆንም ወደፊት ምን እንደሚያጋጥመው አያውቁም።

የምሁሩን ማምለጥ ተከትሎ የኢራን መንግሥት ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጥ አይታወቅም። ኢራን ውስጥ ያሉ ብሪታኒያዊ ኢራናዊያንም ምን ይገጥማቸው ይሆን የሚለውም ሌላ አሳሳቢ ጥያቄ ሆኗል።