ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ፡ የአራት ዓመቷ ሕጻን የዳይኖሰር የእግር አሻራ አገኘች
ሊሊ ዋይልደር የተባለች የአራት ዓመት ሕጻን የባህር ዳርቻ ላይ የዳይኖሰር የእግር አሻራ አገኘች።
የሕጻኗ ግኝት ዳይኖሰሮች እንዴት ይራመዱ እንደነበር ሳይንቲስቶች እንዲያውቁ ይረዳቸዋል ተብሏል።
በዩኬ፣ ዌልስ በሚገኘው ቬል ኦፍ ግላሞርጋን ግዛት በንድሪክስ ቤይ በሚባል የባህር ዳርቻ የተገኘው የዳይኖሰር እገር አሻራ 220 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረ ነው።
የዳይኖሰር አሻራው በአፈር ተሸፍኖ ነበር። ምን አይነት ዳይኖሰር ሲራመድ ኮቴው ታትሞ እንደቀረ ማወቅ ባይቻልም አሻራው አስር ሴንቲ ሜትር ይረዝማል። ይህም ዳይኖሰሩ 75 ሴንቲ ሜትር ይረዝም እንደነበር ይጠቁማል።
የዌልስ ብሔራዊ ሙዝየም የፓሌዎንቶሎጂ ኪውሬተር የሆኑት ሲድኒ ሆዌልስ"ባህር ዳርቻ ከተገኙ ዝርያዎች የተሻለው ነው" ብለዋል።
የአራት ዓመቷ ሊሊ ከአባቷ ሪቻርድ ጋር እየተንሸራሸረች ሳለ ነው አሻራውን ያገኘችው።
እናቷ ሳሊ እንደምትለው፤ ሊሊ አሻራውን ስታይ "አባዬ ተመልከት" ብላ ለአባቷ አሳይታዋለች። ወደ ቤት ሲመለሱ የአሻራውን ፎቶ ለሷ እንዳሳዩዋትም ታስታውሳለች።
"ፎቶው በጣም ድንቅ ነበር። ሪቻርድ ማመን አልቻለም ነበር። ከዚያም ወደ ባለሙያዎች ወሰድነው" ብላለች።
በባህር ዳርቻ አሻራውን ጥሎ ያለፈው ዳይኖሰር ቀጠን ያለና ትንንሽ እንስሳትን የሚያድን እንደነበረ ይታመናል።
ተመሳሳይ አሻራ በአሜሪካ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፤ ሲሎፊዚክስ የተባለ የዳይኖሰር ዝርያ ነው።
በባህር ዳርቻ የተገኘው አሻራ ምናልባትም ወደ አዞ አይነት ከሚጠጉ እንስሳት ጋር ተቀራራቢ ዝርያ ያለው እንደሚሆን ተገልጿል።
ብሔራዊ ሙዝየሙ አሻራውን ወስዶ የቅሪ አካል ምርምር እያደረገበት ይገኛል።
ዳይኖሰሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ምድር ላይ የታዑት ከ230 ሚሊዮን ዓመታተ በፊት ነው። አሻራዎቻቸው የተለያዩ ዳይኖሰሮች እንዲፈጠር ስላደረገው የዝግመተ ለውጥ ሂደታደቸው ያስረዳሉ።
ብሔራዊ ሙዝየሙ እንዳለው፤ የዳይኖሰሩ አሻራ ስለ እንስሳው የእግር ቅርጽ ዝርዝር መረጃ እንዲገኝ ያግዛል።
ይህ አሻራ የተገኘበት አካባቢ በቅሪተ አካል ጥናት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። የዌልስ አጥኚዎች "ብሪትን ውስጥ የዳይኖሰር ዱካን ለመከተል ምርጡ ቦታ ነው" ሲሉ ይጠሩራታል።