አሜሪካና ሜክሲኮን በሚያዋስነው ድንበር የ19 ሰዎች አስከሬን ተቃጥሎ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜክሲኮና አሜሪካን በሚያዋስነው ድንበር የ19 ሰዎች አስከሬን ተቃጥሎ መገኘቱን ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
ግለሰቦቹ ተገድለው የተገኙባት ታማውሊባስ የተሰኘችው ግዛት አስተዳዳሪ እንዳሳወቁት ፖሊሶች አስከሬኖቹን ያገኙት በእሳት በነደዱ ሁለት መኪኖች ውስጥ ነው።
አስከሬኖቹ ላይ በተደረገ ምርመራ በእሳት ከመቃጠላቸው በፊት በጥይት መገደላቸውን ያሳያል።
አካባቢው ነውጠኛ የሚባሉ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች የሚንቀሳቀሱበት ሲሆን በተጨማሪም ስደተኞች ወደ ቴክሳስ ለማቋረጥ የሚሸጋገሩባት ግዛት ናት።
ግለሰቦቹ ስደተኞች ሳይሆኑ እንዳማይቀሩ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አንድ ባለስልጣንን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ሰሜናዊ ታማውሊባስ ግዛት ከዚህ ቀደምም ቢሆን አሰቃቂ በሚባሉ ግድያዎች፣ የሰዎች ደብዛ በመጥፋት የምትታወቅ ሲሆን እነዚህ ክስተቶች በአካባቢው ከሚፎካከሩ የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴ ቡድኖች ጋር የተያያዙ ናቸው።
የሜክሲኮ መንግሥት የአደንዛዥ ዕፅን ለመቆጣጠር በይፋ ጦርነት የሚለውን ዘመቻ በሰፊው ጀምሯል።
ሆኖም የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በርካቶቹ ደብዛቸው ጠፍቷል በሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
በቅርቡ ተቃጥለው የተገኙት ግለሰቦች ቴክሳስን በምታዋስነው ታማውሊባስ ግዛት ካማርጎ ከተማ ነው የተገኙት።
የአስከሬኖቹ ምርመራ ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ አስከሬኖቹ በማይታወቅ ሁኔታ ተቃጥለው በመገኘታቸው እንደሆነ የግዛቲቱ አቃቤ ህግ ማንነታቸውን ለመለየት ያለውን ፈታኝነት አስረድተዋል።
የግለሰቦቹን ማንነት ለማጣራት በተከፈተው ምርመራ ምናልባት ከጓቲማላ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ይሆኑ የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል።
ባለስልጣናቱ የጓቲማላ ቆንሱላን አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አስነብቧል።
በቅርቡ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ በአብዛኛው መነሻቸውን ሆንዱራስ ያደረጉ 7 ሺህ የሚሆኑ የመካከለኛው አሜሪካ ስደተኞች ቡድን ወደ ጓቲማላ ገብተዋል።
በመቀጠልም ሜክሲኮን በመሻገር ወደ አሜሪካም ለመግባት ሰንቀዋል።
በየአመቱም ከመካከለኛው አሜሪካ የሚነሱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ካራቫን ተብሎ በሚታወቀው የጅምላ ቡድን የሚጓዙ ስደተኞች አብዛኛው በእግራቸው ወደ አሜሪካ በአንድ ላይ ይገባሉ።
ስደተኞቹ በአገራቸው ግጭት፣ ፖለቲካዊ መሳደድ፣ ጭቆናንና ድህነትን ሸሽተው እንደሚመጡ ይናገራሉ።
በተለይም እነዚህ አገራት በህዳር ወር ላይ ከፍተኛ ዝናብና አውሎ ንፋስ በቀላቀለው የሆሪኬን ማዕበል መመታታቸው የአገሬውን ዜጎች ሁኔታ አክፍቶታል።
ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከደቡባዊ አሜሪካ ድንበር በሜክሲኮ በኩል የሚገቡ ስደተኞችን ህገ ወጥ በማለት ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘው ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ በሜክሲኮ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስና ኤልሳልቫዶርም አገራት ላይ የስደተኞችን እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠሩ ከፍተኛ ጫና እያሳረፉባቸው ነበር።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የትራምፕን ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲ አስተዳደራቸው እንደሚያሻሽል ቃል ቢገቡም፤ ፖሊሲዎች በአንድ ምሽት ስለማይቀየሩ ስደተኞች ጉዟቸውን እንዳይጀምሩ አስጠንቅቀዋል።












