እስራኤላዊቷ የቀድሞ ርዕሰ መምህር በህፃናት ወሲባዊ ጥቃት ወንጀል ለአውስትራሊያ ተላልፋ ተሰጠች

ማልካ ላይፈር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ታዳጊ ተማሪዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ታደርስ ነበር የተባለችውን የቀድሞ ርዕሰ መምህር እስራኤል ለአውስትራሊያ አሳልፋ ሰጠች።

ግለሰበቧ አውስትራሊያ ሜልቦርን በሚገኝ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በነበረችበት ወቅት በርካታ ታዳጊ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሳለች በሚል አውስትራሊያ ለስድስት አመታት በፈጀ ክርክር ተላልፋ እንድትሰጣት ስትጠይቅ ነበር።

ማልካ ላይፈር የተባለችው እስራኤላዊ ዜግነት ያላት ግለሰብ በአውስትራሊያ ውስጥ በ74 ወሲባዊ ጥቃቶች ክስ የተከፈተባት ሲሆን፤ ወደ ትውልድ አገሯ እስራኤል ያቀናችው ውንጀላዎቹ ሲነሱ በአውሮፓውያኑ 2008 ነው።

ለአመታት ያህል ግለሰቧ ተላልፋ እንዳትሰጥ ስትከራከር የነበረ ሲሆን በዋነኝነት ስታቀርብ የነበረው መከራከሪያ ፍርድ ቤት ለመቅረብ የአዕምሮ ህመምተኛ መሆኗን እንደ ምክንያት ስታቀርብ ቆይታለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ይግባኟን የሰማው በታህሳስ ወር ሲሆን በመጨረሻም ተላልፋ እንድትሰጥ ወስኗል።

ግለሰቧ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ስትል ትከራከራለች።

ተጠቂ ተማሪዎቹን ወክሎ ሲከራከር የነበረው ድርጅት "ለፍትህ ብሩህ ቀን ነው" በማለት የግለሰቧን ተላልፎ መሰጠት አወድሷል።

በ50ዎቹ እድሜ ላይ የምትገኘው ማልካ ላይፈር እዳስ እስራኤል በተሰኘ የይሁዲዎች ትምህርት ቤት ውስጥ ርዕሰ መምህር በነበረችበት ወቅት ህፃናትን ጨምሮ ታዳጊዎችን በመድፈር ክስ ተመስርቶባታል።

ማልካ ላይፈር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች ታጅባ ወደ ቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ ስታቀና የሚያሳይ ፎቶ የእስራኤል ሚዲያዎች ይዘው ወጥተዋል።

ያኔት የተባለው ድረ ገፅ በበኩሉ ግለሰቧ እጇና እግሯ ታስሮ እንደነበርና በአውሮፕላኑም ውስጥ የአውስትራሊያ ባለስልጣናት እንደተቀበሏት ሪፖርት አድርጓል።

ግለሰቧ በፍራንክፈርት፣ ጀርመን በማድረግ ወደ አውስትራሊያ ሜልቦርን ታቀናለች። የእስራኤል ፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም የማልካ ላይፈር ጠበቃ ለአውስትራሊያ ተላልፋ እንደተሰጠች አረጋግጠዋል።

የአውስትራሊያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቃለ አቀባይ ክርስቲያን ፖርተር በበኩላቸው የግለሰቧ ተላልፎ የመሰጠት ሂደት ሙሉ በሙሉ እስሚጠናቀቅ ድረስ መንግሥታቸው ምንም አስተያየት እንደማይሰጥ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የተጠቂዎቹ ተወካይ ቮይስ ኤጌይንስት ቻይልድ ሴክስ አቢዩዝ የተባለው ድርጅት የግለሰቧ ተላልፎ መሰጠትና ለፍርድ መቅረብ ብዙዎች በጉጉት ሲጠበቅቁት የነበረ እንደሆነ አስታውሶ "በሚያሳዝን ሁኔታ ይኸ እንዳይሳካ ሲሰሩ የነበሩ አካላት ነበሩ" ብሏል።

አውስትራሊያ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ግለሰቧ ተላልፋ እንድትሰጣት ስትጠይቅ የነበረ ሲሆን የአዕምሮ ህመም ስላለባት ፍርድ ቤት መቅረብ አትችልም በሚል እስራኤል ጥያቄዋን ውድቅ አድርጋው ቆይታለች።

ነገር ግን ከሁለት አመት በፊት መርማሪዎች ባደረጉት ክትትል ግለሰቧ እቃ ስትሸምት እንዲሁም ገንዘብ ባንክ ስታስቀምጥ በማየታቸው ባለስልጣናቱ በቁጥጥር ስር አውለዋታል።