ኬኒያዊው በሕገ-ወጥ የእንስሳት አካል ዝውውር በአሜሪካ ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተበት

ታትሟል

ኬንያዊው በአሜሪካ ፍርድ ቤት በሕገ-ወጥ የዝሆን እና አውራሪስ ጥርስ ዝውውር ለቀረበበት ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ተከራከረ።

መንሱር ሞሐመድ ሱሩር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ የእንስሳት አካላት አዘዋዋሪ ቡድን ውስጥ አባል በመሆን እና ከ100 በላይ ለሆኑ ዝሆኖች እና አውራሪሶች ግድያ ተጠያቂ ነው ሲል የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል።

ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሕገ-ወጥ እንቅስቃሴው ከ7.4 ሚሊዮን ዶላር ሰብስቧል ይላል።

የእንስሳቱ አካላት በሃውልቶች እና በፊት ቅርጽ በሚሰሩ ቅርጻ-ቀርጾች ውስጥ ተደብቀው እንደሚዘዋወሩ በመንሱር ሞሐመድ ላይ በቀረበው ክስ ላይ በዝርዝር ሰፍሯል።

መንሱር ሞሐመድ ከአንድ ዓመት በፊት በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጥቷል። በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመሰል እና በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ተጨማሪ ክሶች ተመስርተውበታል።

መንሱር የጊኒ፣ የላይቤሪያ እና ኬንያ ዜግነት ካላቸው ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆኑ በኒው ዮርክ እና ደቡብ እሲያ ለሚገኙ ገዢዎች የዝሆን ጥርስ ለመሸጥ ተስማምቷል፤ ለዚህም የስልክ ጥሪ እና የጽሑፍ መልዕክት ማስረጃ ቀርቦባቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ይህን ሕገ-ወጥ ተግባራቸውን የሚያከናውኑት ዋና መቀመጫቸውን ኡጋንዳ በማድረግ ሲሆን፤ በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ጊኒ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሴኔጋል እና ታንዛኒያ ኔትዎርክ ዘርግተው ይንቀሳቀሳሉ ተብሏል።