የዝሆኖች ቆጠራ ከህዋ በሳተላይት እየተካሄደ ነው

ታትሟል

ሳይንቲስቶች በአፍሪካ ስንት ዝሆኖች እንደሚገኙ ለማወቅ ጫካ ለጫካ መሽሎክሎክ አያስፈልግም ብለዋል።

ይልቅ ከሕዋ በሳተላይት ሰው ሰራሽ ልህቀትን በመጠቀም መቁጠር ይቻላል ብለዋል። ይህንንም እያደረጉት ነው።

ከመሬት ወለል 600 ኪሎ ሜትር ርቃ በህዋ ላይ በምትሾረው አንዲት ሳተላይት ነው ምሥሎቹ እየመጡ ያሉት።

ይህ ዝሆንን በሳተላይት የመቁጠር ዘዴ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ አያውቅም። አሁን ግን እስከ 5ሺ ስኬዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታን በአንድ ቀን ብቻ መሸፈን እንደሚቻል ተደርሶበታል።

ዋናው ነገር በዚያ ቀን ደመናማ ጭጋጋማ እንዳይሆን ተስፋ ማድረግ ብቻ ነው።

ይህን ቆጠራ የሚያደርጉት መሣሪያዎች ምሥል ሲቀበሉ 'የትኛው ዝሆን ነው፣ የትኛውስ አይደለም' የሚለውን እንዲያውቁ በአልጎሪዝም ጥበብ የተቀኙ ስለሆነ ሥራውን ቀላል አድርጎታል።

"የኛ ሥራ ለአልጎሪዝሙ ይህ ዝሆን ነው፤ የኛው ግን አይደለም ብለን አንድ ጊዜ መንገር ብቻ ነው፥ ሌላው ቀሪ ሥራ የኮምፒውተሩ ነው" ብለዋል የባዝ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ዶ/ር ኦልጋ ኢሱፖቫ።

"ይህን ስናደርግ እኛ በአይናችን ማየት የማንችላቸውን ዝርዝርና ደቃቃ ነገሮች ጭምር አልጎሪዝሙ እንዲያያቸውና እንዲለያቸው ማድረግ ችለናል" ብለዋል ጨምረው።

እነዚህ ሳይንቲስቶች መጀመርያ ቆጠራ ያደረጉት በደቡብ አፍሪካ አዶ በሚባለው የዝሆን ብሔራዊ ፓርክ ነው።

ይህ አዶ ፓርክ መጀመርያ ሊመረጥ የቻለው በርካታ ዝሆኖች የሚገኙበት ሥፍራ ስለሆነ ነው። በዚያ ላይ ወፋፍራምና ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ ቆጠራው በባህላዊ መንገድ ከባድ ይሆን ነበር።

ከዚህ ቀደም በነበሩ አሰራሮች ትንንሽ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ቅኝት እያደረጉ ቆጠራዎችን በተወሰኑ ቦታዎች በማድረግ ለጠቅላላው አካባቢ ግምታዊ አሀዝ በመውሰድ ነበር።

አሁን ግን ሳተላይት እቅጩን ቁጥር ይነግረናል ብለዋል ሳይንቲስቶቹ።

ምናልባት ይህ የሰው ሰራሽ ልቀት የሳተላይት ዝሆን ቆጠራ ቢሊዮን ዶላር ለሚፈስበት የቤት ለቤት የሕዝብ ቆጠራ የሚውልበት ጊዜ ሩቅ አይሆን ይሆናል።