በቱኒዚያ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሰሩ

በቱኒዝያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በቱኒዚያ አራተኛ ቀኑን በያዘው የአደባባይ ተቃውሞ ፖሊስ በትንሹ 600 ዜጎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ትናንት ሰኞ በርካታ ወጣት ቱኒዚያዊያን በቱኒዝ አደባባዮች በፖሊስ ላይ ድንጋይና ተቀጣጣይ ነገሮችን በመወርወር ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር።

የጸጥታ ኃይሎች በበኩላቸው በተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስና ግፊት ያለው ውሀ ሲለቁባቸው ታይተዋል።

ቱኒዚያዊያን ወጣቶች ለአደባባይ ተቃውሞ ያበቃቸው የኑሮ ውድነት ነው። ከቱኒዚያ ወጣቶች አንድ ሦስተኛው ሥራ አጥ ነው።

በተለይም የኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝን ተከትሎ በቱኒዚያ የምጣኔ ሀብት ምስቅልቅል ተፈጥሯል።

ይህ አዲስ ያገረሸ ተቃውሞ ለአረቡ ጸደይ አብዮት መቀጣጠል እንደ ምልክት የሚታየው ቱኒዚያዊው አልቦአዚዚ የተባለ ወጣት ራሱን ነዳጅ አርከፍክፎ በአደባባይ ካቃጠለ ከ10 ዓመት በኋላ ነው።

የአረቡን የጸደይ አብዮት ተከትሎ አምባገነን መንግሥታት ከመንበራቸው ቢፈነገሉም ኑሮ ግን እምብዛምም ሊሻሻል አልቻለም።

ከሰኞ ወዲህ እየተቀጣጠለ ባለው ተቃውሞ ከቱኒዝ ሌላ በካሰሪን፣ ጋፍሳ፣ ሳውስ እና ሞናስትሪ ወጣቶች አደባባይ ወጥተዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፖሊስ የተመጠነ ኃይል እንዲጠቀምና የታሰሩ ወጣቶችን ሰብአዊ መብት እንዲያከብር ጠይቋል።

አምባገነኑ ንጉሥ ዘይን አል አበዲን ቤን አሊ በሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስተው ወደ ሳኡዲ ከሸሹ በኋላ በመላው የአረቡ ዓለም የዲሞክራሲና የዳቦ ጥያቄዎች ገንፍለው አደባባይ በመውጣታቸው የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ አድርገዋል።

የቱኒዚያውን የዛሬ 10 ዓመት ተቃውሞ ተከትሎ በግብጽ ሆስኒ ሙባረክ፣ በሊቢያ ሙአመር ጋዳፊ መነሳታቸው ይታወሳል።

ሆኖም የጸደይ አብዮት በአረቡ ዓለም ኑሮን አላሻሻለም። የተጠበቀው የለውጥ ተስፋም እንደተዳፈነ ነው ያለው።

አብዯቱ ከተቀሰቀሰ ድፍን 10 ዓመት ሆኖታል። ንጉሥ ቤን አሊ፣ ጋዳፊና ሙባረክ ሦስቱም በሕይወት የሉም።