በአፍጋኒስታን ሁለት ሴት ዳኞች በጥይት ተገደሉ

በአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በአፍጋኒስታኗ መዲና ካቡል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሁለት ሴት ዳኞች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ግድያው የተፈፀመው በዛሬው ዕለት ነው።

ዳኞቹ በወቅቱ ወደ ቢሯቸው እያመሩ እንደነበረና ታጣቂዎች ኢላማ እንዳዳረጉዋቸውም የፍርድ ቤቱ ቃለ አቀባይ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

ዳኞቹ ባደፈጡ ታጣቂዎች ዛሬ ጥዋት ኢላማ እንደተደረጉና፤ ከነሱ ግድያም በተጨማሪ አሽከርካሪያቸውም ቆስሏል ተብሏል።

ግድያው የተፈፀመው በካቡል ቋላ ኤ ፋቱላህ በምትባል አካባቢ ሲሆን ለግድያው ኃላፊነቱን የወሰደ አካል እስካሁን የለም።

በቅርብ ወራት ኢላማ የተደረጉ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ፖለቲከኞች ተገድለዋል። በዛሬውም ዕለት የነዚህ ዳኞች መገደል ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

ባለፈው ወር እንዲሁ ማላላ ማይዋንድ የተባለች የአፍጋኒስታን ጋዜጠኛ በተተኮሰባት ጥይት ከነ አሽከርካሪዋ ተገድላለች።

ከዚህም በተጨማሪ፦

ባለፈው ወር የቀድሞ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ያማ ሲያዋሽ ከሁለት ግለሰቦች ጋር በመኪናው ላይ በተጠመደ ቦምብ ቤቱ አቅራቢያ ተገድለዋል።

  • አሊያስ ዳዬ የተባለች ለሬድዮ ሊበርቲ የምትሰራ ጋዜጠኛ እንዲሁ መኪና ውስጥ በተጠመደ ቦምብ ተገድላለች
  • በአፍጋኒስታን ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የፊልም ዳይሬክተር ሳባ ሳሃር ጥይት የተተኮሰባት ሲሆን ከጥቃቱም ተርፋለች።

በአፍጋኒስታን ለሚዲያ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቀው ናይ የተባለው ድርጅት ባወጣው መግለጫ "የማላላ መገደል በአገሪቷ ያሉትን ጥቂት የሴት ጋዜጠኞች ሞራል የሚገድልና ስራቸውንም በአግባቡ እንዳያከናውኑ የሚያደናቅፍ ይሆናል" ብሏል።

እነዚህን ግድያዎች የሚፈፅመው ታሊባን ነው የሚል ጥርጣሬ ቢያድርም ከታሊባን በኩል የተሰጠ ምንም አይነት መረጃ የለም።

እነዚህ ጥቃቶችና ግድያዎች በተበራከቱበት ወቅት በታሊባን ተወካዮችና በአፍጋኒስታን መንግሥት መካከል ሰላም እንዲፈጠር ዶሃ ላይ ውይቶች እየተካሄዱ ነው።

በተያያዘ ዜና በአፍጋኒስታን ያሉ የአሜሪካ ወታደሮችን ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እያስወጡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያሉትም 2 ሺህ 500 ብቻ ናቸው ተብሏል።

የአፍጋኒስታን ምክትል ፕሬዚዳንት በዚህ ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሜሪካ ወታደሮቿን ማስወጣቷ በግጭቶች ለምትናጠው አገራቸው ተጨማሪ ስጋት ነው ብለዋል።