አፍጋኒስታናዊቷ ጋዜጠኛ ከነ አሽከርካሪዋ ተገደለች

የፎቶው ባለመብት, Presidential Palace
ማላላ ማይዋንድ የተባለችው የአፍጋኒስታን ጋዜጠኛ በተተኮሰባት ጥይት ከነ አሽከርካሪዋ ተገድላለች።
በምስራቃዊ አፍጋኒስታን፣ ጃላላባድ ግዛት ዛሬ ጥዋት ታጣቂዎች በከፈቱባት ተኩስ ነው ህይወቷ ያለፈው።
ጋዜጠኛዋን ለመግደል ባለመው በዚህ ጥቃት አድፍጦ ታጣቂዎቹ ሲሄዱበት የነበረው መኪና ላይ ተኩስ እንደተከፈቱም ተገልጿል። መሃመድ ታሂር የተባለውም አሽከርካሪም ህይወቱ አልፏል።
ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።
በአፍጋኒስታን ዒላማ የተደረጉ ሰዎች መገደል በከፍተኛ ሁኔታ መበራከቱንም በመጥቀስ ከሰሞኑ የአውሮፓ ህብረትና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ሃገሮች ድርጅት (ኔቶ) የውግዘት መግለጫም አውጥተዋል።
ኢኒካስ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ለተባለው ጋዜጠኛ የሆነችው ማላላ ባልታወቁ በተባሉ ታጣቂዎች ተኩሱም የተከፈተባት ወደ ስራ እየሄደች በነበረበት ወቅት ነው።
የግዛቲቷ አስተዳዳሪ ቃለ አቀባይ አታኦላህ ክሆጂያን ለአገሪቷ ሚዲያ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለቀው እንደወጡ ነው።
ማላላ በማህበራዊ ፍትህም ጉዳይ አጥብቃ የምትከራከር ስትሆን ከዚህ ቀደምም በአገሪቷ ውስጥ ሴት ጋዜጠኛ መሆን ስላለው ውጣ ውረድም ትናገር ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት እናቷም ከአምስት አመት በፊት ባልታወቁ ታጣቂዎች እንደተገደሉ የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የጋዜጠኛ ማላላን መገደልንም አስመልክቶ በአፍጋኒስታን የእንግሊዝ አምባሳደር አሊሰን ብሌክ በትዊተር ገፃቸው አውግዘውታል።
"በጋዜጠኛዋ ሞት የተሰማንን ሃዘን እየገለፅን ፤ የማላላንም ሆነ አሽከርከሪዋን መገደል እናወግዛለን። ኢላማ መሆን ይቅር" በማለትም አምባሳደሯ አስፍረዋል።
አክለውም " ሞታቸው ዝም ብሎ ሊታለፍ አይገባውም። ምርመራ ሊከፈት ይገባል፤ ገዳዮቻቸውም ወደ ፍትህ ሊቀርቡ ይገባል"
በቅርብ ወራት ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ፖለቲከኞች በታጣቂዎች ኢላማ ሆነዋል።
- ባለፈው ወር የቀድሞ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ያማ ሲያዋሽ ከሁለት ግለሰቦች ጋር በመኪናው ላይ በተጠመደ ቦምብ ቤቱ አቅራቢያ ተገድለዋል።
- አሊያስ ዳዬ የተባለች ለሬድዮ ሊበርቲ የምትሰራ ጋዜጠኛ እንዲሁ መኪና ውስጥ በተጠመደ ቦምብ ተገድላለች
- በአፍጋኒስታን ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የፊልም ዳይሬክተር ሳባ ሳሃር ጥይት የተተኮሰባት ሲሆን ከጥቃቱም ተርፋለች።
በአፍጋኒስታን ለሚዲያ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቀው ናይ የተባለው ድርጅት ባወጣው መግለጫ "የማላላ መገደል በአገሪቷ ያሉትን ጥቂት የሴት ጋዜጠኞች ሞራል የሚገድልና ስራቸውንም በአግባቡ እንዳያከናውኑ የሚያደናቅፍ ይሆናል" ብሏል።
ከሰሞኑ የአፍጋን ባለስልጣናትና ታሊባን በዶሃ ውይይት እያደረጉ ሲሆን ተኩስ አቁምና የስልጣን መጋራት ስምምነቶች ላይ ድርድርም ይጀምራሉ ተብሏል።












