ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳውያን ከሐይቆች ዳርቻ የሚያገኟቸውን ዓሣዎች እንዳይመገቡ ተከለከሉ
የኡጋንዳ ባለሥልጣናት በአፍሪካ ትልቁ በሆነው የቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ዓሣዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ መሆናቸውን አስታወቁ።
የአገሪቱ ዓሣ ሀብት ሚኒስቴርም ኅብረተሰቡ የሞተ ዓሣ እንዳይመገብ ይልቁንም በሐይቁ ዳርቻ የሚያገኛቸውን ዓሣዎች እንዲቀብር አስጠንቅቋል።
በአገሪቱ ባሉ ሐይቆች ዙሪያ የተለያዩ አካባቢዎቹ ያሉ ነዋሪዎች በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ባሰራጯቸው ፎቶዎች ከቪክቶሪያ ሐይቅ፣ ከኪዮጋ ሐይቅና ከናይል ወንዝ ዳርቻ በደርዘን የሚቆጠሩ ሕይወት አልባ ዓሣዎች በውሃው እየተገፉ እወጡ መሆኑን ያሳያሉ።
ባለስልጣናት ዓሣዎቹ የሞቱት በኦክስጂን መጠን መቀነስ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለው ገምተዋል።
የኡጋንዳ ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች ዓሣዎቹ አለመመረዛቸውን ያሳያል" ብሏል።
ይልቁንም ሰሞኑን በሐይቆቹ ላይ የተከሰቱት አውሎ ነፋሶች የተለያዩ የውሃ አካላት መካከል መቀላቀል እንዲፈጠር በማድረግ በሐይቁ ውስጥ ያለውን የኦክስጂን መጠን እንዲቀንስ ሳያደርግ እንዳልቀረ ሚኒስቴሩ ጥርጣሬውን ገልጿል።
ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በርካታ ዓሣዎች ወደ ሞቱበት አካባቢው ያቀናው የባለሙያዎች ቡድን ሙሉ ሪፖርቱን ከሰኞ በኋላ ይፋ ያደርጋል።
"ሰሞኑን በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅና የእንቦጭ አረም ሳቢያ የተከሰተ የኦክስጂን መጠን መቀነስ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ" ሲሉ የሚኒስቴሩ ባለስልጣን ጆይስ ኢኳፑት ንዬኮ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ እንዳመለከተው በብቸኝነት የተጎዱት ዝርያዎች በብዙ የኡጋንዳ ቤተሰቦች ውስጥ በዋና ምግብነት ተመራጭ የሆነው የናይል ፔርች ዓሣ ዝርያዎች ናቸው።
ከ100 ኪሎ ግራም በላይ ሊያድግ የሚችለው የናይል ፐርች ዓሣ በኦክስጅን እጥረት በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል ዝርያ ነው መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
"በሐይቁ ዳርቻዎች ላይ የሚገኙ የዓሣ አስጋሪዎችና አጠቃላይ ነዋሪው ኅብረተሰብ. . . በብዛት ከሞቱት ዓሣዎች የተነሳ የተፈጠረውን መጥፎ ጠረን ለመቀነስ ዓሣዎቹን እንዲቀብሩ ይመከራል" ብሏል ሚኒስትሩ።
በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ቪክቶሪያ ሐይቅ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ የሚጋሩት የተፈጥሮ ሀብት ነው።
ከሦስት ዓመት በፊት ሳይንቲስቶች የቪክቶሪያ ሐይቅ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ሲሉ አስጠንቅቀው የነበረ ሲሆን፤ ለዚህም በምክንያትነት የተቀመጡት በከፍተኛ መጠን ከሐይቁ የሚጠመደው ዓሣና ብክለት ናቸው።