አምስት የቤተሰቡን አባላት በጭካኔ የገደለው ኬንያዊ ተማሪ ፍርድ ቤት ቀረበ

ታትሟል

አምስት የቤተሰብ አባሉን የገደለው ኬንያዊ ተማሪ ድርጊቱን መፈፀሙን እንዳመነ ተገለፀ።

የኬንያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው የሆነው ይህ ግለሰብ አምስት የቤተሰቡን አባላት እንዴት አቅዶ እንደገደላቸው ለፖሊስ ተናዝዟል።

የ22 ዓመቱ ሳይመን ዋሩንጌ እናቱን፣ ወንድሞቹን፣ አባቱን እና የአክስቱን/የአጎቱን ልጅ ለመደብደብ የብረት ዘንግ መጠቀሙንና ከዚያም በቢላ እንደወጋቸው መናገሩን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ተማሪው ለፖሊስ እንደተናገረው ወላጆቹ "ሰይጣናዊ እና ጨካኝ" እንደነበሩ መናገሩን ዘ ስታር የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

ዋነኛው ተጠርጣሪ ድርጊቱን ለመፈፀም "ኪሊንግ ኢቭ" የተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ ማየቱ እንደገፋፋው መናገሩንም ዘ ስታር ጽፏል።

'ኪሊንግ ኢቭ' የእንግሊዝ አስቂኝና የስለላ ታሪክ ያለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነው።

ሳይመን በድራማው ላይ እንዳለችው ዋና ገጸ ባህርይ በተመሳሳይ አላማውን እንዴት ማሳካት እንደሚችል ኢንተርኔት ላይ መረጃ ሲያፈላለግ እንደነበር ፖሊስን ጠቅሶ ዘ ስታር አትቷል።

በድራማው ላይ ያለችው ዋና ገጸ ባህርይ ከባድ የአዕምሮ ሕመም ያለባትና ጥቃት አድራሽ ናት።

ተጠርጣሪው እንደሚለው ወላጆቹ ይጠሉት እንደነበርና ከጀርባው ሆነው ስለ እርሱ እንደሚያወሩ 'ሲትዝን' የተባለ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ግድያውን በፈጸመበት ወቅት ሁለት እህቶቹ ትምህርት ቤት ሄደው ስለነበረ ከጥቃቱ ለመትረፍ ችለዋል።

ሳይመን የተያዘው ግድያውን ከፈፀመ በኋላ ሸሽቶ ዘመድ ቤት ሊያድር ሲል ፖሊስ ክተትል በማድረግ ደርሶበት ነው።

ሟች እናቱ በኬንያ አንድ ሆስፒታል የሥነ ልቦና ነርስ የነበረች ስትሆን፤ አባቱ ደግሞ በአሜሪካ ነርስ ሆኖ ያገለግል ነበር። ወደ ኬንያ የመጣውም የገናን በዓል ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ ነበር።

መርማሪዎች ከዚህ ቀደም በሌሎች የሩቅ ቤተሰብ አባላት ላይ የተፈፀሙ ግድያዎች ላይ ምርመራ ለማድረግ መዝገቡን እንደገና ከፍተዋል።

ፖሊስ ሳይመን ብቻውን ወንጀሉን ሊፈጽም አይችልም ብሎ የጠረጠረ ሲሆን፤ የተጠርጣሪውን የፍቅር ጓደኛ በቁጥጥር ሥር በማዋል ዛሬ፣ ሰኞ ዕለት ሁለቱም ፍርድ ቤት ቀርበዋል።