የ53 ዓመቱ ጃፓናዊ የእግር ኳስ ኮከብ በተጫዋችነት እንዲቀጥል ኮንትራቱ ተራዘመ

ታትሟል

አንጋፋው ጃፓናዊ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋች ካዙዮሺ ሚዩራ እስከ 54 ዓመቱ ድረስ ለመጫወት የሚያስችለውን ውል በመፈራራም በዮኮሃማ ክለብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት ተስማማ።

የ2021 የጃፓን ሊግ ውድድር ከመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት ሚዩራ የካቲት 26 ቀን 54 ዓመት ይሆነዋል።

የቀድሞው የጃፓን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዮኮሃማን ከ15 ዓመት በፊት የተቀላቀለ ሲሆን ለ17ኛ የውድድር ዘመን ለክለቡ ይጫወታል።

"ለእግር ኳስ ያለኝ ፍላጎትና ፍቅር እየጨመረ ነው" ብሏል።

ሚዩራ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው በብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ ውስጥ 1986 (እአአ) ነበር። በ2017 ደግሞ በ50 ዓመት ከ14 ቀናት ዕድሜው ቴስፓኩሳትሱ ጉንማ ላይ ግብ በማስቆጠር በጃፓን ፕሮፌሽናል ሊግ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረ የአንጋፋው ተጫዋችነት ክብረ ወሰንን ይዟል።

በጃፓን 'ኪንግ ካዙ' [ንጉሥ ካዙ] ተብሎ የሚጠራው ሚዩራ በአገሪቱ ውስጥ በጣም ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርተኞች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በ1993 (እአአ) ጄ ሊግ ሲጀመር የውድድሩ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።

ለጃፓን በ89 ጨዋታዎች 55 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን በክሮሽያና በአውስትራሊያ ከመጫወቱ በፊት በጣሊያን ሴሪ አ ለጄኖዋ ተጫውቷል።

ሚዩራ ክለቡን በአምበልነት አገለግሏል።

ከእግር ኳስ ቤተሰብ የተገኘው ተጫዋቹ ሺዙካ ውስጥ ነው ያደገው። አባታቸው የእግር ኳስ ደጋፊ ሲሆኑ ታላቅ ወንድሙ ያሱቶሺም ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ነበር።

"አባቴ በሜክሲኮው የ1970 የዓለም ዋንጫ ተገኝቶ ከመመልከት ባለፈ እነፔሌ ያሉበት ጨዋታን ቀርጾ ስለነበር እሱን እያየሁ ነው ያደግኩት" ብሏል በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለመጠይቅ።

በሦስት ዓመቱ የተቀረጸውን ቪዲዮ መመልከት ብቻ ሳይሆን "የብራዚል ደጋፊ ሆንኩኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ለመሆን እፈልግ ነበር" ብሏል።

ወደ ብራዚል በማቅናትም ጁቬንቱስ ለተባለው የአገሪቱ እግር ኳስ ክለብ ፈረመ።

ውጣ ውረዶች ቢኖሩበትም በስኬት አለፋቸው።

ከእግር ኳስ ሌላ የሚያስበው መስክ ይኖር እንደሆን ሲጠየቅም "ምንም ሃሳብ አልነበረኝም። ሁሌም የምፈልገው ፕሮፌሽናል ተጫዋች መሆን ነበር። ከባድ ጥያቄ ነው" ሲል መልሷል።

ብራዚል ውስጥ ፔሌ የተጫወተበንትን ሳንቶስን ጨምሮ በተለያዩ የብራዚል ክለቦች በመዘዋወርም መጫወት ችለወል።

ከዚያም ወደ ጃፓን ታዋቂ ተጫዋች ሆኖ ተመለሰ። ጄ ሊግ ሲጀመርም እንደ ጋሪ ሊነክር ያሉ ተጫዋቾችን በመቅደም ኮከብ ሆኖ የውድድር ዓመቱን አጠናቀቀ።

በ1994 ወደ ጄኖዋ በውሰት ሄዶ የተጫወተ ሲሆን በዚህም በሴሪ አው የተጫወተ የመጀመሪያው ጃፓናዊ ለመሆን በቃ።

በ2005 (እአአ) አሁን ለሚጫወትበት ዮኮሃማ የፈረመ ሲሆን ክለቡ በሁለተኛው ዲቪዚዮን ይጫወት ነበር። ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት ወደ ዋናው ሊግ ለማደግ ቻለ።

ሚዩራ በተደጋጋሚ ካለመጎዳቱም በላይ ባለው አካላዊ ብቃት አጠባበቅ ይታወቃል።

ካለው ጠንካራ አካላዊ ብቃት ባሻገር ታዋቂነቱም እየተጫወተ እንዲቀጥል አድርጎታል።

እሱ የሚጫወት ከሆነ እስከ 4000 የሚደርሱ ተጨማሪ ተመልካቾች ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሏል።

እና የ53 ዓመቱ ካዙ አሁንም እንደ ታዳጊዎች በየዕለቱ በፍቅር ልምምዶችን ያከናወናል? ተብሎ ሲጠየቅ "አዎ። አሁንም እግር ኳስ መጫወት ያስደስተኛል። ብራዚል ከነበርኩበት ጊዜ በበለጠ እግር ኳስ መጫወት ያስደስተኛል" ሲል ምላሽ ይሰጣል።