ለዓመታት የጠፋው የግብጽ ታሪካዊ ቅርስ ሲጋራ ካርቶን ውስጥ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, University of Aberdeen
ግብጽ ለዓመታት ጠፍቶብኛል ብላ ስታፈላልገው የነበረው ታሪካዊ ቅርስ ስኮትላንድ አበርዲን ውስጥ በሲጋራ ካርቶን ተጠቅልሎ ተገኝቷል።
የቅርሱ መገኘትም ታላቁ ፒራሚድ ወደነበረበት የቀድሞ ውበቱ እንዲመለስ ያደርገዋል ተብሏል።
የጠፋው ቅርስ ሊገኝ የቻለው አበርዲን ዩኒቨርሲቲ ያሉትን ንብረቶች በሚያጣራበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል። 5 ሺ ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተነገረለት ቅርስ ከእንጨት የተሰራ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ተሰባብሮ ነው የተገኘው። ነገር ግን አሁንም እጅግ ወሳኝ ግኝት እንደሆን ተገልጿል።
ከእንጨት የተሰራው ቅርስ ታላቁ ፒራሚድ በሚገነባበት ወቅት ጥቅም ላይ እንደዋለ እምነት ያለ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1946 ለአበርደን ዩኒቨርሲቲ በስጦታ መልክ ተበርክቶ ነበር።
ነገር ግን ከዛን ጊዜ በኋላ ቅርሱ የት እንደሚገኝ ማወቅ ሳይቻል ቀርቷል።
ቅርሱን ያገኘችው ባለሙያ አቢር ኤልዳኒ ስትሆን በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ ቅርሶች መካከል የእሲያ ቅርሶችን ለመቁጠርና ለማስተካከል ሙከራ በምታደርግበት ወቅት ነው ያገኘችው።
አቢር ትውልዷ ከግብጽ የሆነች ተመራማሪ ስትሆን ላለፉት 10 ዓመታት በግብጽ ካይሮ ሙዚየም ውስጥ ሰርታለች።
'' ቅርሱን ካገኘሁት በኋላ የግብጽ ቅርሶች የሚመዘገቡቡት መዝገብ ላይ ሄጄ ቁጥሩን ሳስተያየው ወዲያው አወቅኩ። ሰዎች ለማስተካከል በሚሞክሩበት ወቅት ተቀላቅሎ እንደጠፋ ገባኝ'' ብላለች።
'' እኔ አርኪዮሎጂ ባለሙያ ነኝ፤ ለበርካታ ዓመታት ግብጽ ውስጥ ቁፋሮ ሳደርግ ኖሬያለው። እንዲህ አይነት ትልቅ ትርጉም ያለው ቅርስ በሰሜን ምስራቃዊ ስኮትላንድ አገኛለው ብዬ ግን አስቤ አላውቅም ነበር'' ስትል በግርምት ተናግራለች።
''ምናልባት ትንሽ እንጨት ሊመስል ይችላል፤ ተሰባብሮም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በጣም ወሳኝ ግኝት ነው። ከታላቁ ፒራሚድ ውስጥ ከወጡ ጥቂት ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ቅርስ ነው''
''በሲጋራ ካርቶን ውስጥ ሳገኘው በጣም ነው የተገረምኩት'' ብላለች።
በሲጋራ ካርቶን ውስጥ ተጠቅልሎ የተገኘው ታሪካዊ ቅርስ በተደረገለት ምርመራ ምናልባት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3341 እስከ 3094 ባሉት ዓመታት ጥቅም ላይ ሳይውል እንዳልቀረ ተገምቷል።












