ሴኔጋል፡ ልጆቻቸውን አውሮፓ ለመላክ ገንዘብ የከፈሉ አባቶች በእስራት ተቀጡ

ታትሟል

የሴኔጋል ፍርድ ቤት ከሰሞኑ ልጆቻቸውን አውሮፓ ለመላክ ለህገወጥ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ ከፍለዋል በሚል ሶስት አባቶችን ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ብሏል።

ሶስቱ አባቶችም የአንድ ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።

አንደኛው ልጅ በያዝነው አመት ጥቅምት ወር ህይወቱ አልፏል።

በሴኔጋል መዲና ዳካር ደቡባዊ በኩል የሚገኘው ምቦር የተባለችው ግዛት የሚገኝ ፍርድ ቤት ነው ቅጣቱን ያስተላለፈው።

አሳ በማጥመድ ስራ የሚተዳደሩት አባቶች የልጆቻቸውን ህይወት አደጋ ውስጥ በመክተትም በሚልም ነው ጥፋተኛ የተባሉት።

ከአንድ ወር እስር በተጨማሪ በእንጥልጥል የሚቆይ ሁለት አመት ያህልም የእስር ጊዜም ተበይኖባቸዋል ተብሏል።

ባህር ሲያቋርጥ ልጃቸው የሞተባቸው ማማዱ ፋዬ ገና በጠለቀ ኃዘን ላይ ናቸው።

የ15 አመቱ ኦስማን በጥቅምት ወር ወደ ካናሪ ደሴት ለማቅናት ከእንጨት በተሰራችው ጀልባ ተሳፍረው ከነበሩ በርካታ መንገደኞች መካከል አንዱ ነው።

ሆኖም በባህር ውስጥ ገብቶ ከሰመጠ በኋላ ህይወቱ እንዳለፈ ተዘግቧል።

አባቱ ለህገወጥ አዘዋዋሪዎች 450 ዶላርም ከፍሏል።

የዱዱም ህልም የነበረው ጣልያን ገብቶ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከሉን ተቀላቅሎ ስልጠና መውሰድ ነበር።

በቅፅል ስሙ ዱዱ ተብሎ የሚጠራው ታዳጊ አውሮፓ ሳይደርስ የሞተ ሲሆን አስከሬኑም ወደ ባህሩ እንደተጣለ ተነግሯል።

የታዳጊው ሞት በሴኔጋል ኃዘን የፈጠረ ሲሆን፤ በቅርቡም ከምዕራባዊቷ አገር ተነስተው ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚሞክሩ ሴኔጋላውያን ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው ተብሏል።

በርካቶችም ፈታኝ የሆነውን ባህርና ውቅያኖስ እንደሚሻገሩም ተገልጿል።

የሴኔጋል ፖሊስ እንዳለው በቅርቡ ብቻ ከ1 ሺህ 500 በላይ ስደተኞችን መመለስ እንደቻለም አሳውቋል።