ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህንድ ተሳቢ እንስሳት መንገድ እንዲሻገሩ ለመርዳት ድልድይ ሰራች
በህንድ የደን ጥበቃ ባለስልጣናት ለተሳቢና አነስ ላሉ እንስሳት መንገድ እንዲሻገሩ ለመርዳት ለየት ያለ ድልድይ ሰርተዋል።
በህንዷ ተራራማዋ ኡታራክሃንድ ግዛት ያለ አውራ ጎዳና ላይ መኪኖች በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚንቀሳቀሱ እንስሳቶች ለመሻገር ተቸግረዋል ተብሏል።
የ27 ሜትር እርዝማኔ ያለውና ከቀርከሃ እንጨት፣ የቃጫ ተክልና ሳር የተሰራው የእንስሳት መሸጋገሪያ ድልድይ በአገሪቷ የመጀመሪያው እንደሆነም የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ናኒታል የምትባል ታዋቂ የቱሪስት መናኸሪያ ግዛት በሚያቀናው በዚህ ጎዳና ላይ እንስሳቱ በከፍተኛ ፍጥነት በሚነዱ መኪናዎች ተገጭተው ህይወታቸው አልፏል።
ባለስልጣናቱም እንስሳቱ በድልድዩ እንዲሻገሩ ለማድረግም ሳርና ቁጥቋጦ እየተከሉም እንደሆነ ተገልጿል።
"በርካታ ተሳቢና ትንንሽ እንስሳት በከፍተኛ ፍጥነት በሚነዱ የቱሪስት መኪኖች ምክንያት ሞተዋል" በማለት በግዛቷ የደን ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ የሆኑት ሼካር ጆሺ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለስልጣናቱ በድልድዩ ሁለቱም መዳረሻ በኩል እንስሳቱ የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ለመቆጣጠርም ያስችል ዘንድ ካሜራ ገጥመዋል።
ድልድዩ በራሱ በአሁኑ ወቅት የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ የሳበ ሲሆን በርካቶችም መኪናቸውን በማቆምና ፎቶዎች ሲነሱም ታይተዋል።
ነገር ግን የደን ጥበቃው ባለስልጣናት ድልድዩ የእንስሳቶቹንም ቀልብ በቅርቡ ይስባል የሚል ተስፋን ሰንቀዋል።
"ይህ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነው፤ ዝሆኖች፣ አቦሸማኔ፣ ጎሽና አጋዘን የመሳሰሉ እንስሳቶች በአውሮ ጎዳናው ሲሻገሩ ቱሪስቶች ከርቀትም ስለሚያይዋቸው ቀስ ብለው ይነዳሉ ወይም ያቆማሉ።
ነገር ግን እባብ፣ እንሽላሊት ሽኮኮ የመሳሰሰሉ በደረታቸው የሚሄዱ ተሳቢ እንስሳትን ማየት አይችሉም" በማለት አንድ የደን ባለስልጣን ለኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ድልድዩ በተሳቢና አነስ ባሉ እንስሳቶች ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና ደህንነታቸውን መጠበቅ የሚያስችል ሁኔታም እንደሚፈጥር ባለስልጣናቱ ተስፋ አድርገዋል።