ስናፕቻት ስኬታማ ደንበኞቼን በየቀኑ 1 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, SNAPCHAT
ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች አንዱ የሆነው ስናፕቻት ‹ስፖትላይት› በተሰኘው አዲስ ገጽታው ላይ እጅግ ተወዳጅ ቪዲዮ ሰርተው ለሚያጋሩ ተጠቃሚዎቹ በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ አለ።
ስናፕቻት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቲክቶክ ጋር ከፍተኛ የገበያ ውድድር ላይ ስለሚገኝ ነው።
ስፖትላይት የተሰኘው የስናፕቻት አዲስ ገጽታ የአልጎሪዝም ቀመርን በመጠቀም ብዙ ሰዎችን ያነጋገረና ብዙዎች መድረስ የቻለ ቪዲዮ ሲኖር ተጠቃሚዎቹ እንዲመለከቱት ይጋብዛል።
ይህም የሚሆነው የተጠቃሚውን የፍላጎት አዝማሚያዎችን መሠረት በማድረግ ነው። አንድ ተጠቃሚ እንዲመለከታቸው የሚጋበዘው ቪዲዮ የሕይወት ዝንባሌውን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው።
ይህ በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያሸልመው አዲስ አሰራር በስናፕቻት ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው ኮከብ ደንበኞቹን ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የስናፕቻት ተጠቃሚን የሚያካትት ነው።
በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር የመሸለሙ ነገር እስከዚህኛው የፈረንጆች ዓመት ማብቂያ የሚዘልቅ ነው። ነገር ግን ደንበኞችን በመሳብ ረገድ የተፈለገውን ውጤት ማምጣቱ ከተረጋገጠ በ2021 ሊቀጥል እንደሚችል ተጠቁሟል።
ተሸላሚ የሚሆኑት ደንበኞች ሰርተው የሚያጋሩት ቪዲዮ ተወዳጅ መሆን ብቻም ሳይሆን በከፍተኛ ፍጥነት መዛመት የሚችል እንዲሆን ይጠበቅበታል።
ስናፕቻት በየቀኑ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚሸልመው ሆኖም ቪዲዮው በስንት ሰዎች ሲወደድ እንደሆነ አላስቀመጠም። ሽልማቱ ለስንት ሰዎች እንደሆነ፣ ይህ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ስንት ሰዎች እንደሚካፈሉትም አልተብራራም።
ሆኖም በዚህ ውድድር ለመታቀፍ ተጠቃሚዎቹ ዕድሜያቸው 16 እና ከዚያ በላይ መሆን ግድ ይላል። የሚጋሩት ቪዲዮዎች አደገኛ እጽና አልኮል መጠጦችን የሚያበረታቱ መሆን የለባቸውም። የስናፕሻት ደንብና ግዴታዎችም ተፈጻሚ ይሆናሉ።
ስናፕቻት ኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ በቀን የተጠቃሚዎች ቁጥር 250 ሚሊዮን ደርሶልኛል ይላል።
ሆኖም የቢዝነስ ተወዳዳሪዎቹ ኢንስታግራምና ቲክቶክ ከፍተኛ የደንበኛ ቁጥር በማስመዝገባቸው ስናፕቻት ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ይህን ከፍተኛ መጠን ያለውን ሽልማቱን እንዳዘጋጀ ተነግሯል።
ቲክቶክ በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካ ገበያው ላይ ዘንድሮ እንቅፋት ቢፈጠርበትም አሁንም ተወዳጅነቱ በመላው ዓለም እንደቀጠለ ነው።












